Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።

(ጥር 05/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት እና ከተገልጋዩ ማህበረሰብ ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይትና ምክክር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ ከፌዴራል የመንግስት ተቋማት ሀላፊዎች፣ ከግዥ ዳይሬክተሮችና ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የመንግስት ትልቁ በጀት ለግዥ አገለግሎት የሚውል በመሆኑ ይህን በጀት በስርዓት መምራትና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ትልቅ ሀግራዊ ሚናን እየተወጣ የሚገኝና ውጤታማነቱን ለማስቀጠል ላለፉት ስድስት ወራት ማሻሻያዎች ሲደረጉ እንደቆዩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለመጨመር ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመንና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችን ከመከለስ ጀምሮ ተጨባጭ ስራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከመተግበር አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መተግበር መቻሉ ስርዓቱ በውጤታማነት እየቀጠለ እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል። በገለጻው ሁሉም ክልሎች ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል እየተሰራ እንዳለም ተብራርቷል። ባለስልጣኑ ከመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP System) በተጨማሪ የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ ቁጥጥር (e- Fleet Management)፣ ዲጂታል ደብዳቤ መላላኪያ (Letter Management)፣ ዲጂታል አስተያየትና ጥቆማ መስጫ (Digital suggestion box) እና የመሳሰሉት ስራዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይ እንደዋሉ ተገልጿል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ከአነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ሲሆን የሪፎርም ስራዎች የተቋሙን ራዕይ እና ተልዕኮ ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውና የሪፎርም ስራዎችም በውጤታማነት እየተከናወኑ እንዳሉ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትንና ሌሎች የአሰራር ስርዓቶችን በውጤታማነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዋና ዳይሬክተሯ እና ሌሎች የባለስልጣኑ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *