ባለስልጣኑከፌዴራልባለበጀትመስሪያቤቶችሃላፊዎችጋርውይይትእያካሄደነው።

(ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከአሰራር ስርዓት ማዘመን፣ ከዲጂታላይዜሽን እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ አበይት የሪፎርም ስራዎችን አስመልከቶ ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክቡር አቶ ፈቃዱ ሆረታ እንደገለጹት፤ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን በርካታ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን አከናውኗል። ተቋሙ የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ስርዓትን በፌዴራል ደረጃ ሙሉ በሙሉ ከመተግበሩ ባሻገር አሰራሩን ወደ ክልሎች ለማውረድ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ክቡር አቶ ፈቃዱ አክለውም ባለስልጣኑ ከመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ስርዓት በተጨማሪ የበይነ-መረብ ትምህርት (e-Learning)፣ የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም ቁጥጥር (e-Fleet) እና ሌሎች የዲጂታል ስራዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ስራ ላይ እንዳዋለ አመላክተዋል።
ከዲጂታላይዜሽን በተጨማሪ ባለስልጣኑ ውጤታማ የኦዲትና ክትትል ስራዎችን፣ የይግባኝና ጥፋተኝነት ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት የሪፎርም ስራዎችን በላቀ ሁኔታ እያከናወነ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ክቡር አቶ ፈቃዱ በመድረኩ ላይ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሰራሩን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ብዙ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰው በመድረኩ ላይ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሪፎርም እና የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ዘላቂነት ያለው የግዥ ስርዓት ስትራቴጂክ እቅድ (Sustainable Procurement) እና አደገኛ ቆሻሻዎች አያያዝ፣ አጠባበቅ፣ አጓጓዝ እና አወጋገድ ማኑዋል ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው አመላክተዋል።
በአሁኑ ሰዓት የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኢጂፒ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን ውይይቱ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚቀጥል ይሆናል።





0 Comments