The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም፣በንብረት አስተዳደር፣በተሽከርካሪ አያያዝ እና በነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከፍትህ አካላት እና ከሚዲያ ተቋማት ለተውጣጡ የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከግንቦት 22—26/2008ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡
የሥልጠናው ዓላማም በዋናነት ግዥ ከፍተኛዉን የመንግሥት በጀት ስለሚይዝ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውና የተሻለ የግዥ ስርዓት ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለዉ መሆኑንና ግልጽ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የመንግስት ግዥና  ንብረት አስተዳደር ማስፈን እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አቶ ነጋሽ ቦንኬ በመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸም ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣አቶ ታደሰ ከበደ በመንግስት ግዥ አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት የግዥ ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ባለሙያ፣አቶ ወርቁ በዛብህ በመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ባለቤት የሌላቸው የመንግስት ንብረቶች ከፍተኛ ባለሙያ ስልጠናውን የሰጡ ሲሆን ስለመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፤ ስለመንግስት ግዥ ዓላማና መርሆዎች፣ ስለ  ግዥ ዕቅድ፣ስለተፈቀዱ የግዥ ዘዴዎች፣ስለመደበኛ የጨረታ ሠነዶች፣ስለጨረታ አከፋፈትና ግምገማ፣ ስለምክር አገልግሎት ግዥ፣ ስለውል አሰተዳደር፣ ስለ ዋጋ ማስተካከያ፣ ስለ ዋና ዋና ተግባርና ኃላፊነቶች፣ ከግዥ ባለሙያዎችና ከአቀራቢዎች  የሚጠበቅ ሥነ ምግባር እንዲሁም ስለመንግስት ንብረት አያያዝ፣ትርጓሜ እና ዓላማ ስለመንግስት ንብረት አስተዳደር ተግባራት፣ ስለሰቶክ አስተዳደር፣ስለ ቋሚ ንብረት አስተዳደር፣ ስለ መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሚና፣ስለ አጠቃላይ ቆጠራ እንቅስቃሴና የመዝገብ ዝግጅት ሂደት፣ ለቋሚ ንብረቶች ዋጋ ስለመመደብ እና ስለ ቋሚ ንብረቶች የእርጅና ቅናሽ በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ሰልጣኞች በቆይታቸዉ ስልጠናው ጥሩ አቅም እንደፈጠረላቸውና የነበረባቸውን ክፍተት ለመሙላትና ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በየመ/ቤታቸው ሲመለሱ  ወደ ተግባር ለመለወጥ አጋዥ እንደሚሆንላቸው ገልጸዋል፡፡
ለአምስት ቀናት በቆየው በመንግስት ግዥ አፈጻጸም፣በንብረት አስተዳደር፣በተሽከርካሪ አያያዝ እና በነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ከፍትህ አካላት እና ከሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በሴቶች አመራርና ራስን መቻል፣ በኤች አይቪ/ኤድስ እና ስነ-ተዋልዶ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን በሴቶች አመራርና ራስን መቻል፣ በኤች አይቪ/ኤድስ፣የቤተሰብ ምጣኔና ሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ግንቦት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ ሥልጠና ሰጠ፡፡
አቶ ደረጀ ተክሌ በኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ኢንስቲተዩት ሌክቸረር በሴቶች አመራርና ራስን መቻል በሚል ርዕስ ስልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ በራስ መተማመን ማለት ምን ማለት ነው? በራስ የሚተማመን ሰው ምን ዓይነት ሰው ነው? በራስ መተማመን ማለት ሃሳብና ፍላጎትን በነጻነት መግለጽ፣መብትና ግዴታን ማወቅ፣ የሌሎችን ስብዕናን ማክበር እንዲሁም በራስ መተማመን መገለጫው በለውጥ ማመን እንደሆነና በራስ መተማመን ደግሞ ከትምህር ቤትና ከህይወት ልምድ እንደሚገኝም ገለጻ አድርገዋል፡፡  
በመቀጠልም አሰልጣኙ ሴቶችና አመራር በሚል ስለ አመራር ምንነት፣የአመራር ክህሎትና መገለጫው፣ የአመራር ከህሎት ከየት እንደሚጀምር፣እንዴት ብቁ መሪ መሆን እንደሚቻል እንዲሁም ሴቶች የማህበረሰቡ ግማሽ አካል እንደሆኑ፣ሴቶች ለአመራር ብቁ ስለመሆናቸው፣ የአመራር ክህሎት በሴቶች ዘንድ አና ሴቶችን በአመራር ለማበረታት የአመለካከት ለውጥ ላይ ስለመስራት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሲስተር ሂሩት አለማየሁ ከኤች አይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በበኩላቸው ስለ የቤተሰብ ምጣኔና ሥነ ተዋልዶ፣ ስለ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ ሰለ ሥርጭቱ ሁኔታ፣ስለ አጋላጭና ተጋላጭ ባህሪያት፣የመጋለጥ ሁኔታ ከሴቶች አንጻር፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዙሪያ ስላለው መረጃ እና የህበረተሰቡ ሚና የሚለውን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
አሰልጣኟ ስለ ሥነ-ተዋልዶና የቤተሰብ ምጣኔን በሚመለከት ስለ ሴትና ወንድ ሥነ-ተዋልዶ አካላት፣ የቱኩረት ነጥቦች ከሥነ-ተዋልዶ አንጻር ትምህርትም በተለያዩ የወጣት ማዕከላትና ጤና ጣቢያ እንደሚሰጥ ገለጻ አድርገዋል፡፡

25ኛው የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓል ተከበረ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ከመንግሥት የግዥና የንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ የሚከበረውን የግንቦት 20 በዓልን ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አዳራሽ አከበረ፡፡
የዕለቱ የክብር ዕንግዳ ክቡር አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር በበዓሉ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የበዓሉ ዓላማ የሩብ ክፍለ ዘመን ስኬቶቻችን አሁን ለደረስንበት ደረጃ እንዴት እንዳበቁን በማሳየት ያሉብንን ችግሮች የሚፈታ ድሎቻችንን የሚያጎለብትና የሚያስቀጥል የህዝብ መነሳሳት፣የተሻለ መግባባትና የባለቤትነት መንፈስ መፍጠር መሆኑን  አስታውቀው ለበዓሉ ታዳሚዎች ለመድረኩ የተዘጋጀውን ፅሁፍ በጥሞና እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡  
አቶ ተስፋዬ ብርሀኑ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር በዓሉን በማስመልከት ከማሽቆልቆል ጉዞ ወደ ዕድገት ምዕራፍ ሩብ ምዕተ ዓመት የትግልና የድል ጉዞ በሚል ርዕስ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡   
ም/ዋና ዳይሬክተሩ ህዝብ የተጠቀመበት የ25 ዓመታት የዕድገት ጉዞ፣ልማት ተስፋፍቶ ማሽቆልቆል የተገታበት ሩብ ምዕተ ዓመት፣ጉዞን የገታ የመሰረተ ልማት የተስፋፋበት ሩብ ምዕተ
ዓመት፣ጉዞን የገታ ዲሞክራሲ እውን የሆነባቸው ሀያ አምስት ዓመታት፣ጉዞን የመግታት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ መልካም አስተዳደር የታየባቸው ሀያ አምስት ዓመታት እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነታችን የዳበረበት ሩብ ምዕተ ዓመት በሚሉት ርዕሶች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ለተመዘገቡ ድሎች ያበቁን ዋና ዋና ምክንያቶች የትክክለኛ አመራር፣ፈፃሚ ሀይልና የአፈፃፀም አቅጣጫ ውጤት መሆኑ፣ርዕዮተ አለማዊ ትጥቅ የጨበጠ ድርጅት የመራው እንቅስቃሴ መሆኑ፣ብቃቱ የተመሰከረለት ድርጅት የመራው ለውጥ መሆኑ፣ሁሉ በብስለትና በፅናት ባለፈ ድርጅት የተመራ የተሀድሶ ጉዞ መሆኑና ሌሎች ለተመዘገቡ ድሎች ያበቁን ዋና ዋና ምክንያቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ከበዓሉ ታዳሚዎች በተነሱት የተለያዩ አስተያየቶች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶ በበላይ አመራሮች ለበዓሉ የተዘጋጀው ኬክ ከተቆረሰ በኋላ ከብሄራዊ ሎተሪ የተላኩት በርካታ ሎተሪዎች ላይ ሽያጭ ተከናውኖ የዕለቱ ስብሰባ ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ተጠናቋል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው የ2008 ዓ.ም 25ኛው ዓመት የግንቦት 20 በዓል ላይ የሶስቱም መ/ቤቶች አመራሮች፣ኃላፊዎችና ሠራተኞች በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳሬክቶሬት

ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራርና ሙስናን መከላከል በሚመለከት ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሥነ-ምግባር  የተሞላ አመራርና ሙስናን የመከላከል ተግባርን በሚመለከት ለኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከግንቦት 11—12/2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡
አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ መክፈቻው ንግግር ላይ እንደተናገሩት  ሥልጠናው ለኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሰጥ የተፈለገበት ምከንያት በመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሠረት የአገሪቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ከሚፈስባቸውና በዚያው ልክ የመንግስት ገንዘብ ለብክነትና ለሙስና የተጋለጡ ናቸው ተብለው ከተፈረጁት የሥራ ዘርፎች አንዱ የመንግስት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር በመሆኑና ይህም የተዘረጋውን የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ሥርዓት ተከትሎ የስራ ዘርፉ ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ሆኖ በጥራትና በሚፈለገው ጊዜ እንዲከናውንና ለሀገሪቱ ልማት እና መልካም አስተዳደር የበኩሉን አሰተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የመንግስት ግዥ የሚፈጸመው በእያንዳንዱ ባለበጀት መ/ቤት እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ግዥ ፈጻሚ መ/ቤት ሕጎችን በማክበር በመልካም ሥነ-ምግባር መፈጸም ያለበት ሲሆን፣ ኤጀንሲያችንም በየመ/ቤቱ የሚከናወነውን የግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓቱን ጠብቆ ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ከሚያደርጉት አካላት ጎራ ስለሆነ የተሰጠውን ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ከሙስና በጸዳ ሁኔታ የሙያውን ሥነ-ምግባር በመከተል ተግባራቱንና ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡
አቶ ወንድይራድ ሰይፉ በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል የቡድን አሰተባባሪ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት እና ፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በአንድ ተቋም ሩጫና ጥረት የሚቀረፍ ሳይሆን አጠቃላይ በሆነ መልኩ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመቀየር በሚያስችል ሁኔታ በየደረጃው  ያሉ ተቋማትና ማህበረሰቡ በተደራጀ መልኩ የሚያደርጉትን የባለቤትነት ስሜት የታከለበት ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቴክኒካል አድቫይዘር ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ስለሥነ-ምግባር ምንነት? ለምን ሥነ-ምግባር  የተሞላ አመራር ላይ እናተኩራለን? ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራር ማለት ምን ማለት ነው?ምንስ ይጠይቃል? ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራር መርሆዎችና ክህሎቶች ምንድን ናቸው? መገለጫና ባህሪዎቹ እንዲሁም የሚገጥሙትስ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራር፣ሙስናን የመከላከል ተግባር ቁርኝታቸውና አመልካች ነጥቦቹ  እና ሌሎች አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ነባራዊ ምሳሌ በመስጠት ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል ፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለ2 ቀናት በቆየው በሥነ-ምግባር የተሞላ አመራርና ሙስናን መከላከል በሚመለከት በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በሚመለከት ውይይት ተደረገ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች የ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና  በቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት በመስጠት መከናወን የሚገባቸው ስትራቴጂያዊ ግብ ተኮር ተግባራትን በተመለከተ የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዓላማ ባለፈው የ2008 በጀት  ዓመት  የመጀመሪያው  6 ወራት  የዕቅድ አፈጻጸም ምን ይመስላል? በቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት በመስጠት መከናወን የሚገባቸው ተግባራትን በተመለከተ የጋራ መግባባትን ለማምጣት  መሆኑን ለስብሰባው ታዳሚዎች ገልጸው፣ የውይይቱም ተሳታፊዎች ጥያቄ በመጠየቅና አስተያየት በመስጠት በንቃት መከታተልና መሳተፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አቶ መሥፍን መኮንን የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር ኤጀንሲው የመንግስት ገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ ማስገኘት እንዲያስችል እና በዘርፉ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ግልፅ፣ ፍትሀዊና በውድድር ላይ የተመሰረተ የመንግስት ግዥ አፈጻጸምን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም የመንግስት ንብረት አስተዳደር ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ አሰራሮችን ከሪፎርምና ከመልካም አስተዳደር ተግባራት ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ኤጀንሲው በ2008 በጀት ዓመት  ለማከናወን ያቀዳቸው ስትራቴጂያዊ ግብ ተኮር ተግባራት በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ከፍሎ መመልከት እንደሚቻል እነሱም የሪፎርምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፆኦ ማበርከት የሚያስችሉ እና በአዋጅ 649/2001 የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች የሚያሳኩ የሚያስችሉ ግብ ተኮር ተግባራትን ማከናወን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወራት የመደበኛ ሥራዎች አፈፃፀም በአራቱ ዕይታዎች ከተገልጋይ፣ ከፋይናንስ፣ ከውስጥ አሠራር፣ ከመማማርና ዕድገት እይታዎች አንጻር በየዳይሬክቶሬቱ የ2008 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን በሚመለከት እንዲሁም ሰለአጋጠሙ ችግሮችና ስለተወሰዱ የማስተካከያ አሰራሮች ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎ የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል ፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የኤጀንሲው የ2ዐዐ8 የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ውይይት ላይ ከ80 በላይ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

More Articles...