The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው የፈዴራል ቷቋማት በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው ከስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና እና ከፍትህ አካላት ለተዉጣጡ ባለሙያዎች በአጠቃላይ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ከየካቲት 1 እሰከ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሥልጠና ሰጠ፡፡  
የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ትዕግስት ደበበ ሥልጠናዉን የሰጡ ሲሆን፤  ሰለመንግስት ግዥ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለመንግስት ግዥ ልዩ ባህሪያት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች፣ ስለመንግስት ግዥ ዓላማና መሠረታዊ መርሆዎች ትከከለኛ መጠን፣ጥራት፣ምንጭ፣ዋጋና ጊዜ መሆናቸውን፣ ከአድልዎ ነፃ ሰለሆነ አሠራር፣ግልፅነት፣ ለሕዝብ ተጠያቂነት፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ሰለማበረታት፣ስለልዩ አሰተያየት፣ ስለመንግሰት ግዥ አጠቃላይ ገፅታ፣ስለግዥ ምንነት፣ ዓይነቶችና ሂደት፣የመንግሰት ግዥ ስለሚመራባቸው ሕጋዊ ሠነዶች፣ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ላይ ያለው አዋጅና ዋና ዋና ይዘቶች ዘርዘር ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመንግስት ግዥ አስተዳደር ከፍተኛ የግዥ ሥልጠና እና ሙያዊ ድጋፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታደሰ ከበደ ደግሞ ስለተፈቀዱ የግዥ ዘዴዎች ስለ ግልጽ ጨረታ፣ውስን ጨረታ፣ሁለት ደረጃ ጨረታ፣የመወዳደሪያ ሃሳብ በመጠየቅ፣በዋጋ ማቅረቢያ፣ከአንድ አቅራቢ ሰለሚፈጸም ግዥ፣የግዥ ዘዴ ስሚወሰንበት ሁኔታ በግዥ ዓይነት መጠን ውስብስብነትና ስለአቅራቢዎች ቁጥር ውስንነት በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ከግዥ ባለሙያዎችና አቅራቢዎች ስለሚጠበቅ ስነ-ምግባር፣በመንግስት ግዥ  ውስጥ ሊኖር ስለሚገባ ስነ-ምግባርና በግዢ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ከሥራ ኃላፊነታቸው አንጻር የጥቅም ግጭትን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡

በመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማሰወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነጋሽ ቦንኬ  በበኩላቸዉ አቅራቢዎች በመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ እና የመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ የሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት አጠቃላይ ገጽታ ሥነ-ሥርዓቱና ሰለሚመራባቸው ህጎች፣ አቅራቢዎች በመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች፣ ምክንያቶችና የአቀራረብ ሥነ-ሥርዓት፣ስለግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ ስለሚያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው፣የመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ የሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት  ሰለሚቀርብባቸው ና ስለማይቀርብባቸው ሁኔታዎች፣በኤጀንሲው የሚደረግ የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት፣በአቅራቢዎችና በመንግስት መ/ቤቶች በኩል ሰለ የሚታዪ ግድፈቶች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው መ/ቤቶች ባዘጋጀዉ በሥልጠና ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች አሰተያየቶች የተጠየቁ ሲሆን፤ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥaል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ተሰጠ


የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከጥር 29-30 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሥልጠና ሰጠ፡፡
አቶ ትዕግስት ደበበ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሻሻል ላይ ያለውን የመንግሥት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አዋጅ ዋና ዋና ገጽታዎችን በሚመለከት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያትም በአፈጻጸም የታዩ የአሠራር ጉድለቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤ መሆናቸውን፣ የአገሪቱን የልማት ግቦችን ለማሳካት በመንግሥት ግዥ የአገር ውስጥ ተወዳዳሪዎችን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ፣ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ የተሟላ ለማድረግ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ማካተት የግድ መሆኑ፣እንዲሁም የአዋጁን አወቃቀር በማስተካከል ለአፈጻጸም የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ መሆኑንና ስለማሻሻያው አዋጅ ዓላማና በአዋጁ ረቂቅ የተደነገጉ ዋና ዋና ለውጦችን  አስረድተዋል፡፡
አቶ ታደሰ ከበደ በመንግስት ግዥ አስተዳደር ከፍተኛ የግዥ ሥልጠና እና ሙያዊ ድጋፍ ባለሙያ ደግሞ በበኩላቸዉ በግዥ አፈጻጸም መመሪያ እና ደንቦች ይዘት እና የተፈጻሚነት ደረጃን በሚመለከት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ስለግዥ ዘዴዎች፣ስለመደበኛ የጨረታ ሰነዶች፣ስለአቅራቢዎችና የግዥ ባለሙያዎች፣ የግንባታ ዘርፍ ሥራ፣የምክር አገልግሎትና ስለኢትዮጵያ የግዥ የህግ ማዕቀፍና ሌሎች የአሰራር ዘዴዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡  
አቶ ነጋሽ ቦንኬ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የፌዴራል መንግስት ግዥ በሚመራባቸው የህግ ሰነዶችን በሚመለከት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ሰለፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001፣ለዚሁ አዋጅ አፈጻጸም ዓላማ የወጣውን የግዥ አፈጻጸም መመሪያ እና የመንግስት የግዥ አፈጻጸም ማንዋል፣ ተሻሽለው ስለወጡ መደበኛ የጨረታ ሰነዶች፤ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ሂደት አቅራቢዎች ያላቸው መብትና ግዴታዎች ምን ምን እንደሆኑ፣ በግዥና ንብረት አሰተዳደር አዋጅና በግዥ አፈጻጸም መመሪያው ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ስለተሰጡ መብቶች፣ በአቅራቢዎች በኩል ሰለሚታዩ ግድፈቶች፣ በፌዴራል መንግስት ግዥ ላይ አቅራቢዎች በመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ እና የመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ የሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት ዙሪያ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
አቶ ሙሉ አድገህ በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የአገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ ባለሙያ ሰለሰነዱ ዓላማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማበረታታት የወጣውን የመንግስት ግዥ መመሪያን መሠረት በማድረግ በልዩ አስተያየት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በተሰራው ስራ ኢንተርፕራይዞች ያጋጠማቸውን ችግር የመለየትና የመፍትሄ ሃሳብ በማሰቀመጥ፣የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መሆኑንና ጥቃቅንና  አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በጨረታ ሂደት ያጋጠሙ  ችግሮችና  መፍትሄዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በተካሄደዉ ሥልጠና ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች አሰተያየቶችም የተነሱ ሲሆን፤ ለተነሱ ጥያቄዎችና አሰተያየቶች መልስ ተሰጥaል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት


29ኛው የዓለም ኤች አይቪ ኤድስ እና 26ኛው የጸረ-ፆታ ጥቃት ቀን ተከበረ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እና ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን የዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን እና የጸረ—ጾታ ጥቃት ቀን ህዳር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ በድምቀት አከበረ፡፡

አቶ ይገዙ ዳባ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት የዓለም ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ እና በአገራችንም “አሁንም ትኩረት ለኤች. አይ.ቪ መከላከል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ እንደሚገኝና የዚህ በዓል ዓላማም በሽታው እያደረሰ ያለውን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ጉዳት ለመከላከል፣ ብሎም ለማስቆም እንዲሁም በበሽታው የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና ለመንከባከብ አድሎ እና መገለልን በማስወገድ አገራችንን ጨምሮ የዓለም መንግሥታትና መላው የዓለም ሕብረተሰብ ስለበሽታው ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ በዘንድሮው ዓመት የዓለም ኤድስ ቀንና የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በጋራ ሲከበር ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል የኤች.አይ.ቪ ስርጭት መጠንን ለመቀነስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከግምት በማስገባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ከዋኒ ይብራ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የጤናና ሥነ—ምግብ ፕላን ከፍተኛ ባለሙያ በዓለም ለ29ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኤድስ ቀን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ የሰጡ ሲሆን፣ በየዓመቱ ቀኑ ሰለሚከበርበት ምክንያት፡- ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ በኤች. አይ.ቪ እና ኤድስ የተጎዱትን ወገኖች ለመርዳትና ለማበረታታት፤ ጥናቶችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብና መረጃን ለመስጠት፤ የባለቤትነትን ስሜት ለመፍጠር መሆኑንና በአገር ደረጃም የ2008 ዓ.ም. ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ህክምና አገልግሎት አፈጻጸም ከዕቅድ አንጻር ምን ይመስል እንደነበር፣ አሁንም ያሉት ተግዳሮቶችና ስጋቶች ምን እንደሆኑ እና የባለድርሻ አካላት /የመንግስት ሴክተሮች/ ሚና ጎልቶ መውጣት እንዳለበትና ይህም ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ወ/ሮ ትብለፅ ቡሽራ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ  የሆኑት በዓለም ለ26ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጸረ—ጾታ ጥቃት ቀንን በሚመለከት ጾታዊ ጥቃትና አካላዊ ሥነ-ልቦና ምንድነው? ጾታን መሰረት አድርገው በህብረተሰቡ፣ በቤት ውስጥ እና በስራ አካባቢ ስለሚያጋጥሙ ጥቃቶች፣ ስለ ህግ ማዕቀፍ ጾታዊ ጥቃትን በሚመለከት ከህገ መንግስቱ አንጻር እየቃኙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል፡፡

ለግማሽ ቀን የቆየው የዓለም የኤድስ ቀን እና የዓለም አቀፍ የጸረ—ጾታ ጥቃት ቀን በስነ-ፅሁፍና ኤች.አይቪን በሚመለከት በቃል ምስክርነት በመታጀብ የደመቀ ሲሆን የሶስቱም መ/ቤት ሃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን በሚመለከት በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚተገበርበት ማስፈጸሚያ ዕቅድ ላይ ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት የግዥና የንብረት ማሰወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚተገበርበት ማስፈጸሚያ ዕቅድን በሚመለከት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አሰተባባሪነት ለኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከጥር 9—12/2009 ዓ.ም. በመንግስት የግዥና የንብረት ማሰወገድ አገልግሎት አዳራሽ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ዶ/ር አብርሃም ተከስተ  የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ ዓላማውም የፐብሊክ ሰርቪሱ የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥቱን ባህርያትና የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና በውል ተገንዝቦ ለላቀ የህዝብ አገልጋይነት  እንዲነሳሳ ማድረግ፣ በአገልግሎት የሚስተዋሉ በአስተሳሰብና በተግባር የህዝብ አገልጋይነትና ውጤታማነት የሚጎዱ ዝንባሌዎችን በዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል በማስተካከል የቀሪ GTP II ዓመታት ተግባራትን በላቀ ደረጃ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ዝግጁነትና ተነሳሽነት መፍጠርና በአገራዊ የለውጡ ሂደት ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ አቅጣጫ ላይ ግልጽነት እንዲዳብር በማድረግ በአመራሩና በሠራተኛው መሀከል ጠንካራ መተማመንና መደጋገፍን መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ሚኒስተሩ በዓለማችን የሚታዩ መንግሥታትን በአጠቃላይ በ3 በመመደብ እንደሚቻል ገልጸው ስለ ሊበራል ካፒታሊሰታዊ መንግስት፣ ስለ ዕዝ አኮኖሚ ሥርዓት መንግስትና ስለ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ምንነትና መገለጫዎች ያስረዱ ሲሆን፤ ከነዚህም ለምን ልማታዊ መንግሰት እንደተመረጠም ሲያብራሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እድገት ጎዳና የሚያደርሰ እንደሆነና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ ህዝባዊ ወገናዊነት ያለውና ልማት የህዝቡ ጉዳይ ነው ብሎ የሚያምን መንግሥት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሥልጠናውም የቡድን ወይይት ክፈለ ጊዜ የነበረ  ሲሆን፣ በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለ3 ቀናት በቆየው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚተገበርበት ማስፈጸሚያ ዕቅድን በሚመለከት ስልጠና ላይ የአጄንሲው የበላይ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡

 

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ


የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመተባበር በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር ላይ ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡ወ/ሮ መስከረም ግርማ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የጤና ባለሙያ የሆኑት ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ ስለ ጡት ካንሰር ምንነት፣ መንስኤዎች፣ ምልክቶች፣ለጡት በሽታ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ ልማዶች፣ ሊደረጉ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች፣ የራስን ጡት ስለመመርመር ዘዴ፣ ስለጡት ካንሰር ማረጋገጫ ምርመራዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡አሰልጣኟ በዓለማችን በጡት ካንሰር በሽታ በዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ሰዎች የሚጠቁ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ወደ 75 በመቶ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸውንና በካንሰር በሽታ ምክንያት ለሞት ከተዳረጉ ሰዎች 64.9 በመቶ የሚሆኑት በታደጊ አገሮች የሚገኙ መሆናቸውን የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም አሰልጣኟ ስለማህጸን ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ መንሰኤዎች፣ ምልክቶችና የማህፀን ካንሰርን ለመከላከል ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ያመጣሉ ተብለው የሚታመኑ ህዋሶችና ድርጊቶች፣ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ፣ ሲጋራ ማጬስ እና ሌሎች ምክንያቶች የሚጠቀሱ መሆኑን ገልጸው፣ሲጋራ አጫሽነትም በዚሁ በሽታ የመጠቃት እድልን ከፍ እንደሚያደርግ እና የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ በየትኛውም የዕድሜ ክልል  ውስጥ ሊከሰት የሚችል በሽታ ሲሆን በአብዛኛው በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ሴቶች ለዚህ  በሽታ እንደሚጋለጡ አስረድተዋል፡፡በመጨረሻም አሰልጣኟ ከተሳታፊዎች ለተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሰጡና አሰተያየትም የተቀበሉ ሲሆን ሰልጣኞችም ከስልጠናው ጥሩ ገንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ የሁለቱም መ/ቤት ሴት ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

More Articles...