The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

ከክልልና የከተማ አስተዳደሮች ተቆጣጣሪ አካላት ጋር ቋሚ የጋራ የምክክር መድረክ ጉባዔ ተካሄደ

የመንግሥት የግዥና የንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ በክልልና የከተማ አሰተዳደሮች የመንግሥት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት መካከል 7ኛው ዙር ቋሚ የጋራ የምክክር መድረክ ጉባዔ ግንቦት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ አካሄደ፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገራችን የተጀመረውን ፈጣን ልማትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ በመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ውስጥ ሊከሰት የሚችል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን በአገር ደረጃ ከምንጩ ለማድረቅ እና በምትኩ ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሠራርን እና መልካም አሰተዳደርን ለማስፈን፣ በሀገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ሰራዊት ግንባታ ከዳር ለማድረስና የህዝብ ክንፍን በመለየት በጋራ ቋሚ መድረክ በመገናኘት ከምንግዜውም በበለጠ ተቀናጅተን መሥራት እንደሚጠበቅብን ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ ሃላፊዎች ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን እየተሻሻለ የሚገኘውን የመንግሥት ግዥና ንብረት አሰተዳደር አዋጅ ያካተታቸውን ጉዳዮች፣ ያለበትን ደረጃ፣የአዋጅ ማሻሻያ ጥናቱ ዋና ዋና ዓላማዎች፣ በጥናቱ ውጤት መሠረት የቀረቡ ዋና ዋና የማሻሻያ ኃሳቦች እና ማሻሻያውን ማድረግ ያስፈለገባቸው ምክንያቶች በመንግሥት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ የግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በመቀጠልም ስለ 2008 ዓ.ም. የቁልፍ የግዥ አመልካቾች አፈጻጸም ሂደትና የወረዳ ኦዲት ሽፋን በአራቱ ለሙከራ የተመረጡ ክልሎች በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደርኤጀንሲ የግዥ አስተባባሪና የስልጠና አማካሪ፣ የ2008 ዓ.ም. የቁልፍ የግዥ አመልካቾች አፈጻጸም ሂደትና የ2009 ዓ.ም. የወረዳ የግዥ አፈጻጸም ሂደትና የሽፋን ደረጃ በትግራይ ክልል የግዥና ንብረት የስራ ሂደትና በኦሮሚያ የግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክቶሬት እንዲሁም በፌዴራል መስሪያ ቤቶቸና በልማት ድርጅቶች ያለአገልግሎት ተከማችተው ስለሚገኙ የተለያዩ ንብረቶች የተደረገ የዳሰሳ ጥናትን በሚመለከት በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ቀርቧል፡፡
በወይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች አሰተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ ለጥያቄዎቹም መልስ ተሰጥል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው የምክክር መድረክ ውይይት ላይ የክልል ተቆጣጣሪ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት


የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በከይዘን አተገባበር ዙሪያ ውይይት አካሄደ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጥምረት በከይዘን አተገባበር ዙሪያ  ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
በዕለቱ የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድማሱ ማሞ አጠቃላይ የኤጀንሲውን የከልቡ (ከይዘን ልማት ቡድን) የ5ቱ ማዎችና የብክነት ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ የሚገኝበት ደረጃና የተጣሉትን ግቦች በከይዘን የትግበራ ዕወጃ ያቀረቡ ሲሆን፣ የከይዘን 5ቱ ማዎች ማለትም ማጣራት፣ ማስቀመጥ፣ ማጽዳት፣ ማላመድና ማዝለቅን በተመለከተ ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ መኮንን ያኢ የኢትዮጵያ የከይዘን ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር ከይዘንን መተግበር ያለብን ይተግበር ስለተባለ ብቻ ሳይሆን ሀገርንና ህብረተሰቡን ለመለወጥ ያለውን ጉልህ ሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከይዘንን ተግብረው ስኬታማ የሆኑ ሀገራት ተሞክሮ በመጥቀስ ሁሉም ሰው በመ/ቤት ደረጃም ብቻ ሳይሆን በግላችን ከቤታችን ጀምሮ እንኳ ብንተገብረው ውጤታማ ያደርገናል በማለት ሁሉም አካል  ለከይዘን ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የኤጀንሲው ሰራተኞች ከይዘን የለውጥ መሳሪያ እንጂ ተጨማሪ ሸክም መስሎ እንዳይታየውና በቆራጥ መንፈስ የታቀደውን የከይዘን ዕቅድ መተግበር አለበት ብለዋል፡፡ ከይዘንን በትክክል ብንጠቀምበት መ/ቤቱን ከመለወጥ አልፎ ሃገርን የሚለውጥ መሳሪያ እንደሆነ ገልጸው፣ ትልቁ ጉዳይ የአመለካከት ጉዳይ በመሆኑ የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮችም ከይዘንን ለመተግበር ያላቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን አሰታውቀዋል፡፡
ከይዘን የሚያስገኘውን ጥቅም በትክክል በማጤን ለትግበራው ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ውይይቱም እንደተጠናቀቀ የኤጀንሲው ሰራተኞችና ሃላፊዎች ከይዘንን በይፋ ለመተግበር ያላቸውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት ለመግለጽ የጋራ የጽዳት ዘመቻ በማካሄድ የዕለቱን የውይይትና የጽዳት ፕሮግራም አጠናቀዋል፡፡    
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በሚመለከት ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው የኤጀንሲው ሀላፊዎች እና ሠራተኞች የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ሚያዝያ 17/2009 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡   
አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዋና ዓላማ የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸማችን ምን ይመስላል? በቀሪዎቹስ ሁለት ወራት እንዴት አሟልተን እንጨርሳለን? ከመልካም አስተዳደር፤ ከለውጥ ትግበራ፣ ከተገልጋይ፣ ከፋይናንስ፣ ከውስጥ አሠራር፣ ከመማማርና ዕድገት እይታዎች አንፃር ምን አቀድን? ምን ሰራን? ያጋጠሙ ችግሮችና መፍተሄዎቻቸውስ ምን መሆን አንዳለባቸው ለይተን በማውጣት የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ማተኮር አለብን በማለት የዕለቱን ውይይት ከፍተዋል፡፡
በመቀጠልም በኤጀንሲው ስር ያሉ የየዳይሬክቶሬቶቹ ዳይሬክተሮች የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸማቸውን በአራቱ ዕይታዎች ማለትም ከተገልጋይ፣ ከፋይናንስ፣ ከውስጥ አሠራር፣ ከመማማርና ዕድገት እይታዎች አንጻር ዕቅድና አፈፃፀማቸውን በማነጻጸር ገለፃ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የየዳይሬክቶሬቶቹ ዳይሬክተሮች  ያጋጠማቸውን አንኳር አንኳር የሆኑ ችግሮች፣ ስለተወሰዱ የማስተካከያ አሰራሮችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡ ከተነሱ አበይት ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-
ኤጀንሲው በቂ ያልሆነ የሰራተኞች የስራ ክፍል (የቢሮ ማነስ) መኖሩ፣
የኤጀንሲው የደሞዝ ደረጃ ከስራው ጋር ተመጣጣኝ ያለመሆን (አነሰተኛ ክፍያ መሆኑ)
ከዚህ ችግር አንፃር ነባር ባለሙያዎችን ይዞ ማቆየት ካለመቻሉም በላይ አዳዲስ ባለሙያዎችን ከውጭ ለመቅጠር (በዝውውር) መሟላት አለመቻሉ ከፍተኛ የኤጀንሲው ችግሮች መሆናቸው ተነስቷል፡፡
በተነሱት ጥያቄዎች ላይ የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ በቂ ማብራሪያ በመስጠት የጋራ ግንዛቤ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በቀጣይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጡ የሚገቡ ተግባራት መካከል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነጥሎ ማውጣትና መፍትሄዎቻቸው ላይ በማተኮር፣ የስነምግባር እሴቶችን በማጎልበት ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን በመታገል የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል በማለት የዕለቱን ውይይት ቋጭተዋል፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የኤጀንሲው የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ውይይት ላይ የኤጀንሲው የበላይ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

41ኛው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) በሚመለከት ስብሰባ ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትና ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ጋር በመተባበር 41ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) በሚመለከት የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

አቶ አክሊሉ ገብረስላሴ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሚኒሰትሩ ጽ/ቤት ኃላፊና አማካሪ በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የሴቶች የረጅም ጊዜ የነጻነት ትግል ውጤት የሆነው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ በተለያዩ ትምህርት ሰጪ ፕሮግራሞች ‹‹የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ ለህዳሴያችን መሰረት ነዉ!›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ መሆኑንና በአደጉት እና በታዳጊ ሀገሮች ሰለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ አመጣጥና አከባበር በዝርዝር ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ነጠሩ ወንድወሰን በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሥርዓተ ጾታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር ባቀረቡት ጽሁፍ ስለ ሴቶች ጭቆና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በተለያዩ የተዛቡ አመለካከቶችና የባህል ተፅእኖዎች ምክንያት በህበረተሰቡ ውስጥ የሚገባቸውን ቦታ ይዘው መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው በሀገር ልማት ውስጥ ሊያደርጉ የሚችሉትንና የሚገባቸውን ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚያስችሉ አሰራሮችና ድርጊቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም በአህጉር ደረጃ አፍሪካ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተነፈጉባት እንደነበር፣ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የአፍሪካ ሴቶች አህጉሪቱን ከአውሮፓዊያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ያበረከቱት እና የተጫወቱት ሚና ትልቅ እንደነበርና በአገራችንም በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ሥርዓቶች  የተፈራረቁባትና  ሥርዓቶቹም የየራሳቸው ባህሪ የነበራቸው ሲሆን፣በመሰረታዊ ይዞታቸው በህብረተሰቡ ጥያቄዎች አፈታትና በሴቶች ጥያቄዎች አፈታት ላይ ተቀራራቢነት እንደነበራቸው አሰረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ወይዘር በላይ በቤተሰብ መምሪያ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ሴቶቸን እያጠቃ ስላለው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ አጋላጭ ሁኔታዎች፣ ምልክቶቹ፣  ምርመራ ሰለማድረግ፣ ግንዛቤ ስለመፍጠርና ስለህክምና መንገዱ በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ተምሳሌት ከሆኑ ሴቶች መካከል የሕግ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የህይወት ልምዳቸውን ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ጥያቄዎችን በመጠየቅና አሰተያየት በመስጠት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በቆየው የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ስብሰባ ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ተጠሪ መ/ቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

ከፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶችና ከማዕቀፍ ግዥ አቅራቢ ደርጅቶች ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማሰወገድ አገልግሎት ጋር በመተባበር ከፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች፣ከአቅራቢ ደርጅቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
አቶ ይገዙ ዳባ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ለመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከተሰጠው ተልዕኮ ውስጥ የመንግስት መ/ቤቶች የሚጠቀሙባቸውን ተመሳሳይ ዕቃዎችና አገልግሎቶች እንዲሁም አገራዊ ስትራቴጂካዊ ጠቃሜታ ያላቸውን ዕቃዎችና አገልግሎቶች ከከፍተኛ ግዥ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ በሚያስገኝ መልኩ ግዥ መፈጸምና ውሳኔ የተሰጠባቸውን የመንግስት መ/ቤቶች ንብረቶችን በተቀላጠፈ አኳኋን በተመጣጣኝ ዋጋ በሽያጭ መፈፀም እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ይገዙ ዳባ አገልግሎቱ ግዥን ከመፈጸም ጎን ለጎን የመንግስት መ/ቤቶች ውሳኔ ሰጥተው እንዲወገዱ ለአገልግሎቱ የሚላኩት የተለያዩ ንብረቶችን በማስወገድ ረገድም የተለያዩ ንብረቶችን ሽያጭ በመፈፀም ከ470 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግስት ግምጃ ቤት ፈሰስ ማድረጉንና በዚህ ግማሽ ዓመትም የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን፣ልዩ ልዩ ጎማዎችን፣ዕቃዎችንና ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በማስወገድ በድምሩ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የውይይቱ ዓላማ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን የዉይይት መድረኩ የተዘጋጀ መሆኑን፣በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ችግር በመንግስት ግዥና ንብረት አከባቢ የሚስተዋለዉን የግንዛቤ ክፍተት ዙሪያ መንግስት ትኩረት የሰጠው ጉዳይ መሆኑን፣በአብዛኛው የሚታየው የአፈጻጸም ችግር ለመቅረፍ ኤጀንሲዉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን፣ባለበጀት መስሪያ ቤቶች አመታዊ የግዥ ዕቅድ ስለማቅረብ፣ ለመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ ስለተሰጠው ኃላፊነት፣የተጠያቂነት ሥርዓት ስለመዘርጋት የሚሉትን እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ዉይይት አድርገዋል፡፡
በቀረበዉ የውይይት ሰነድ ዙሪያ በ2009 የመጀመሪያዉ ግማሽ በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ በዝርዝር ገለጻ ተደርገዋል፡፡
ለአንድ ቀን በቆየው የምክክር መድረክ የሁለቱም መ/ቤቶች ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የፌዴራል መንግስት አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

More Articles...