The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

በቁልፍ የግዥ አፈፃፀም መለኪያ/(KPI) ዙሪያ ከክልል ተቆጣጣሪ አካላት ጋር አዉደ ጥናት ተካሄደ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ ከክልል ተቆጣጣሪ አካላት፣ ከክልል ዕድገት ተኮር ቢሮዎች እና ከተመረጡ   የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች ጋር በቁልፍ ግዥ አፈጻጸም መለኪያ ዙሪያ እንዲሁም በወረዳ የግዥ ኦዲት አፈፃፀምን በሚመለከት ከሐምሌ 2 እስከ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ቶሚ ኢንተርናሽናል ሆቴል አዉደጥናት አካሄደ፡፡አቶ ነቢዩ ኮከብ በመንግስት ግዥና ንብረት አሥተዳደር አጄንሲ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ የሆኑት በአዉደ ጥናቱ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት የዚህ አዉደ ጥናት ዋና ዓላማ የመንግሥት ግዥና ንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ በቁልፍ ግዥ አፈፃፀም አመልካቾች ትግበራ በተለይ በአራቱ ክልሎች (በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ እና በአማራ) ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት አበረታች ቢሆንም በሰባቱ የተመረጡ የፌደራል መ/ቤቶች እና በሌሎቹ ክልሎች ያለው አፈፃፀም ደካማ ስለሆነ ምክንያቶቹን ነቅሶ በማውጣት በመፍትሔዎቹ ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ ቁልፍ የግዥ አፈፃፀም አመልካቾችን በመተግበር ረገድ የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ክልሎች  ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ማድረግ እና የክልል ወረዳዎች የግዥ ኦዲት አፈፃፀም የሚገኝበትን ደረጃ በጋራ በመገምገም ለወደፊቱ አቅጣጫ በማስቀመጥ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ፀጋዬ አበበ በመንግሥት ግዥና ንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ የአለም ባንክ ፕሮጀክት የግዥ አስተባባሪና የስልጠና አማካሪ ስለቁልፍ ግዥ አፈፃፀም መለኪያ አመልካቾች ፅንሰ ሃሳብ ምንነትና አስፈላጊነት፣ ስምምነት በተደረሰባቸዉ የቁልፍ ግዥ አፈፃፀም መለኪያዎች፣የቁልፍ ግዥ አፈፃፀም አመልካቾች ሂደት አጠቃላይ ገጽታ እና የአራቱ ክልሎች ቁልፍ የግዥ አፈፃፀም መለኪያ ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች እንድሁም የወረዳ ግዥ ኦዲት አፈፃፀምን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡ከሁሉም ክልል ተቆጣጣሪ አካላት፣ከክልል ዕድገት ተኮር ቢሮዎች እና ከፌዴራል     ቁልፍ የግዥ አፈፃፀም መለኪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በሙከራ ደረጃ ከተመረጡ ባለበጀት መ/ቤቶች ጋር ለሚደረግ አዉደ ጥናት ላይ የተሳተፉ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዉ፤ ለተነሱት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለሶስት ቀናት በቆየው የቁልፍ ግዥ አፈፃፀም መለኪያዎች /KEY PROCUREMENT INDICATORS/ ለተካሄደዉ አዉደ ጥናት ዉይይት መድረክ ላይ ከ100 በላይ የክልል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በግዥ አፈጻጸም እና የንብረት አስተዳደር ዙሪያ የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠና ተሰጠ

በፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በግዥ አፈጻጸም እና የንብረት አሥተዳደር ዙሪያ እንዲሁም ደረጃ ለወጣላቸው ዕቃዎች የተዘጋጀውን ስፔሲፊኬሽን በሚመለከት ሰኔ 24 ቀን 2011ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ የአቅም ማሳደጊያ ሥልጠና ተሰጠ፡፡አቶ ነቢዩ ኮከብ በመንግስት ግዥና ንብረት አሥተዳደር አጄንሲ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ የሆኑት በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ዋና ዓላማ በመንግሥት ግዥና ንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ እና በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ትብብር ደረጃ የወጣላቸውን በመ/ቤቶች በጋራ የሚፈለጉ ዕቃዎችን ግዥ በመፈጸም ረገድ ልንከተላቸው የሚገቡ አሰራሮችን እና ደረጃ ለወጣላቸው ዕቃዎች የተዘጋጀውን ስፔሲፊኬሽን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያሉ ችግሮችን እና ክፍተቶችን በመለየት መ/ቤቶች ግዥ በሚፈጽሙበት ጊዜ የተዘጋጀውን ስፔሲፊኬሽን በመጠቀም የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃን የሚያሟሉና ደረጃቸውን የጠበቁ ዕቃዎችን በመግዛት በመንግስት ገንዘብ የሚገዙ ዕቃዎች ከወጣባቸው ገንዘብ ጋር ተመጣጠኝ የሆነ ፋይዳ እንዲያገኙ በማድረግረገድ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እነደሆነ ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም የዋና ዳይሬክተር አማካሪው ደረጃ  በወጣላቸው ዕቃዎች አተገባበር ዙሪያ ግዥ ፈጻሚ መ/ቤቶች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ በመንግሥት ግዥ ዘርፍ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ አፈጸጸም እንዲኖር ማስቻል መሆኑን አብራርተዋል፡፡አቶ ወርቁ በዛብህ በመንግሥት ግዥና ንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ ባለቤት የሌላቸው ንብረቶች ቡድን መሪ ስለግዥ ምንነት፣ ስለግዥ ዓይነቶች ስለመንግስት ግዥ መርሆዎች፣ ስለአጽዳቂ ኮሚቴ ተግባርና ኃላፊነት፣ ስለ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ ተግባርና ኃላፊነት  ስለግዥ ዕቅድ፣ ስለተፈቀዱ የግዥ ዘዴዎች እና ስለ ግልጽ ጨረታ ዝርዝር አፈጻጸም ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡አቶ ይስማው ጅሩ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ ደረጃ ምንድነው? ደረጃ ለምን ያስፈልጋል? ስለጥራት መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ፣ ደረጃን መተግበር ስለሚያስገኘው ጥቅም፣ ስለጥራት የተሳሳተ ግንዛቤዎች፣ ደረጃ አውጪዎች በዋናነት ሰለሚኖራቸው ድርሻ እና ስለኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አመሰራረት በዝርዝር አብራርተዋል፡፡አቶ ይልማ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃዎች ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት የግዥ ትግበራ ስለመጠቀም፣ ስለግዥ ፈጻሚዎቸ ሚና፣ የደረጃ መነሻዎች በአማካሪ ቢጠና ምን ችግር አለው? በመንግሥት ግዥ ማዕቀፍ ውስጥ እንዴት ግዥ ይፈጸማል? ትግበራ  በማን ይረጋገጣል? ትግባራዊነቱ ምን ላይ እነደሆነና ስለ ግዥ ደረጃዎች ዓላማ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው አፈጻጸም እና የንብረት አሥተዳደር ዙሪያ እንዲሁም ደረጃ ለወጣላቸው ዕቃዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ከ100 በላይ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት


በመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ፕሮጀክት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚተገበረው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (Electronic Government Procurement)ን በሚመለከት ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች ሰኔ 1 እና 2 ቀን 201 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት ፕሮጀክቱን የማስተዋወቅ ሥራ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የኤክትሮኒክ ግዥ ሪፎርም ማለት ከወረቀትና ከተለመደው አሰራር በመውጣት የአገራችን የግዥ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኮምፒውተር የታገዘ የግዥ ዘዴ ለመፈጸም መሸጋገር መሆኑን አስረድተዋል፡፡በመቀጠልም ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ ይህንን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ፕሮግራም ማካሄድ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የመንግስት ግዥ ሙያ እንደመሆኑ በሙያተኞች መመራት ስላለበት እና በኤጀንሲው ሰራተኞች መካከል ዕኩል የኤክትሮኒክ ግዥን መረጃ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል፣ የኤክትሮኒክ ግዥን የሚተገብሩ ባለቤቶችም የኤጀንሲው ሰራተኞች በመሆናቸው እኩል ግንዛቤ ለመፍጠር የታሰበ በመሆኑን እና የኤጀንሲው ሰራተኞች በሙሉ ለኤሌክትሮኒክ ግዥ ባለድርሻ አካል በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘዉም ኤጀንሲዉ ከሚያካሂዳቸዉ ሪፎርም ስራዎች ዉስጥ የግዥ እና የንብረት ፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠና፣የቁልፍ ግዥ አመልካቾች፣የኤሌክትሮኒክ ግዥ እና አዋጅና መመሪያ መሻሻያ ሥራዎችም እየተሰሩ መሆናቸዉን አክለዉ ገልፀዋል፡፡በዉይይት መድረኩ ላይ የኤጀንሲዉ አመራሮች ስለመንግስት ግዥ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የመንግስት ግዥ ዕድሎች እና ሥጋቶች፣ የኤሌክትሮኒክ ግዥን ከመተግበር የሚገኙ ዋና ዋና ጥቅሞች ዉስጥ የመንግስትን ግዥ ስርዓትና አሰራር ግልፀኝነትን ማሳደግ፣በግዥ ሂዳት ዉስጥ ጊዜን በማሳጠር ጥራትን ማሻሻል፣የገንዘብ የመግዛት አቅምን ማሳደግ እንዲሁም በግዥና በሻጭ መካከል ያለዉን መተማመን በማሻሻል ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡በሥልጠናው ላይ ሰራተኛው በቡድን ተከፋፍሎ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣በወይይቱም ላይ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለሁለት ቀን በቆየው የመንግስት የኤክትሮኒክ ግዥ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ኤጀንሲው ሰራተኞች በሙሉ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢፌድሪ የመ.ግ.ን.አ.ኤ.የህዝብ ግንኑነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ ሠራተኞች የመልካም አሰተሳሰብ መጀመርያ የሆነውን አካባቢን የማጽዳት ተግባር አካሄዱ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሰራተኞች የመልካም አሰተሳሰብ መጀመርያ የሆነውን አካባቢን የማጽዳት ተግባር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያከናውነው የሚገባውን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን አካባቢን የማጽዳት ዘመቻን በመደገፍ ግንቦት 9/2011 የኤጀንሲውን ቅጥር ግቢ በማጽዳት ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ግንባር ቀደም በመሆን፣ ሠራተኛውን በማበረታታ እና አብረው ቆሻሻን በማጽዳት ተግባር ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡የተለያዩ የኤጀንሲው ዳይሬክቶሬቶች ዳይሬክተሮችና የኤጀንሲው ሠራተኞች ቆሻሻን በማጽዳትና መተላለፊያ መንገዶችን ዘግተው የተቀመጡ ነገሮችን በማንሳት አካባቢው ለእይታ እንዲመችና ጽዱ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም የመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ “አካባቢን ከቆሻሻ ውስጣችንን ከቂምና ከጥላቻ እናጽዳ” ከሚለው መርህ በመነሳት ይህ የጽዳት ዘመቻ ቆሻሻን ብቻ ሳይሆን አእምሮአችንን ለማጽዳት አመላካችና ጥሩ ምሳሌ መሆኑን እንዲሁም ውብና የበለጸገች ከተማን ተባብረን መፍጠር እንዳለብን መልዕክት አሰተላልፈዋል፡፡

በፌ.መ.ግ.ን.አ.የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለተመረጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በግዥና ንብረት አሰተዳደር፣ በመንግስት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ ከሚያዚያ 10-12/2011 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ግዥ ውስን የሆነውን የመንግስት ሃብት ለሁሉም ዜጎች በተቻለ መጠን ዕኩል ሊከፋፈል የሚችልበትን ሥርዓት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ ከአገራዊ በጀት ከ65-70% ግዥ ላይ የሚውለውን የመንግስት በጀት አብዛኛው ሊጠቀም የሚችልበትንና ለሁሉም ዕኩል ዕድል የሚሰጠውን ግልፅ የጨረታ ዘዴ በመጠቀም ለዜጎች ዕኩል የማወዳደር ዕድል ስንሰጥ መሆኑን በሚገባ ገልጸዋል፡፡ወ/ሮ መቅደስ ብርሃኑ በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ ስለ መንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ ግዥ ምንድነው? ዓላማውስ? ግዥ እንዴትና ለምን ይታቀዳል? ስለ ግዥ መረጣ ዘዴ፣ ሰለጨረታ ግምገማ፣ ስለዋጋ ማስተካካያ እንዲሁም የመንግስት ግዥ ዋና ዓላማው ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘት (Value for Money) መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በመቀጠልም አሰልጣኟ ስለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ፣ በአፈጻጸም የታዩ የአሰራር ችግሮች፣ አቅራቢዎች ስለሚያቀርቡት ቅሬታ፣መ/ቤቶች ስለሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት፣ ስለአቤቱታ ማጣራት ሥነ-ሥርዓት፣ስለ ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ እና ስለ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ በዝርዝር ገልጸዋል፡፡አቶ ደበበ ማሞ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የንብረት አስተዳደር ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት በመንግስት ንብረት አስተዳደር ዙሪያ እና ሚና ስላላቸው አካላት፣ስለመንግስት ተሽከርካሪዎች ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም፣ ስለመንግስት ንብረት አወጋገድ፣ ለመንግስት ንብረት አስተዳደር ዓላማ፣ ስለ ንብረት ማስወገጃ ዘዴዎች፣ስለንብረት አሰተዳደር የስራ ተግባርና ሃላፊነት፣ ስለንብረት መለያ ቁጥር እና ስለ ቋሚ ንብረት የእርጅና ቅናሽን በሚመለከት ሥለጠና ሰጥተዋለ፡፡አቶ ዘለቀ ታፈሰ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ስለግዥና ንብረት ኦዲት ሂደቶች፣ኮምፒሊያንስ እና ፕርፎርማንስ ኦዲት፣ ሰለኦዲት ዕቅድ አዘገጃጀት፣ ስለ ኦዲት ስምምነት፣ በግዥና ንብረት ፈጻሚ መ/ቤቶች በኦዲት ወቅት ስለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣ በመ/ቤቶች ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት ስላለው የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ቀናት በቆየው ሥልጠና ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፣ በርካታ ጥያቄዎችም ተነስተው ለጥያቄዎቹም በኤጀንሲው አመራሮች እና በአሰልጣኞቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

More Articles...