The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ግዥና የንብረት አስተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት የጋራ ምክክር መድረክ ተካሄደ

በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት መካከል የሚደረገው 6ኛ ዙር የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አዳራሽ ታህሳስ 20 ቀን 2007 ዓም .ተካሄደ፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገራችን በተጨባጭ እየታየ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት ለማረጋገጥ በመንግሰት ግዥ አፈፃፀም እና በንብረት አስተዳደር ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመከላከል እንዲሁም ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሰራርና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በየበኩላችን የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከምንጊዜውም በበለጠ ተቀንጅቶ መስራት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

Read more...

የኤጀንሲው እና የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የምክክር መድረክ ተካሄደ

በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በክልልና የከተማ አስተዳደር የገ/ኢ/ል/ቢሮዎች መካከል የሚደረገው 6ኛ ዙር የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ በሂልተን ሆቴል አዳራሽ ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓም .ተካሄደ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት መንግስት ለሚያንቀሳቅሰው  ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ማስፈፀሚያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኘው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከተሰማሩ ዜጎችና ኩባንያዎች በግብርና በቀረጥ መልክ ከሚሰበሰበው ገንዘብ መሆኑን በመጥቀስ፤ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የንግዱ ህብረተሰብ በማለት የምንጠራው አምራቹ፣አከፋፋዩ፣በግንባታ፣በምክር አገልግሎት እና ሌሎች፣በፋይናስና በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩ አካላትና ዜጎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የመንግስት ሀብት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ መንግስት በሥርዓቱ ላይ በየጊዜው ማሻሻያዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ አምራችና አቅራቢዎች ከውጭ አገር ተጫራቾች ጋር ሲወዳደሩ ልዩ አስተያየት ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱ አንዱ ማሳያ መንገድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Read more...

በመንግስት ቋሚ ንብረት እና ስቶክ አስተዳደር ላይ ሥልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግስት ቋሚ ንብረት አስተዳደር  እና በስቶክ አስተዳደር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ሥልጠና ለሚመለከታቸው የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከታህሳስ 6-10 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰጠ ፡፡
የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደበበ ማሞ እና የጥናትና መረጃ ትንተና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደምሱ አብዲ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዓላማ ውጤታማና የስቶክ አስተዳደር መርህንና ሥርዓትን እንዲረዱ፣የስቶክ አስተዳደር ተግባራትን የማከናወን አቅም ለማዳበር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የንብረት አስተዳደር እና የስቶክ አስተዳደር ህግጋትንና ሥርዓትን ጠንቅቀው እንዲያወቁ ግንዛቤ ለመስጠት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኞቹ አጠቃላይ ስያሜን፣ስቶክ መለየትና መመደብን፣መቀበል እና መፈተሽን፣ወጪ ማድረግን ፣የስቶክ መዛግብት የሂሳብ ሪፖርትን፣ስቶክ ቆጠራና ቁጥጥርን፣ክምችትን፣ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦችና መርሆዎችን፣በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ቋሚ ንብረቶች የአስተዳደር መዋቅር፣የመጀመሪያ አጠቃላይ ቆጠራ እንቅስቃሴና የመዝገብ ዝግጅት ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡

Read more...

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግሥት ግዥ ዙሪያ ሥልጠና ሰጠ

የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ ዙሪያ ከሁሉም የፌዴራል መ/ቤቶች ለተውጣጡ ሰልጣኞች ከህዳር 29 እስከ ታህሣሥ 3/2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ለአምስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡

ሥልጠናው በዋናነት በፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በግዥ ሥርዓትና አጠቃቀም ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍና ግዥ ከፍተኛውን የመንግሥት በጀት ስለሚይዝ ጥንቃቄ አንደሚያስፈልገው እንዲሁም ከሠልጣኞች ልምድ ለመውሰድና ከአሰልጣኙ መ/ቤት ደግሞ ቲዎሪን በመውሰድ ሁለቱን በማቀነባበር የተሻለ የግዥ ሥርዓት ለማስፈን አብሮ መማማር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡

አሰልጣኞቹ አቶ ታደለ ነጋሽ የግዥና ንብረት የኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ አቶ ዘለቀ ታፈሰ ከፍተኛ የግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ባለሙያ እና አቶ ታደሰ ከበደ ረዳት የግዥ ጥናትና መረጃ ትንተና ባለሙያ ስለ መንግሥት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ የመንግሥት ግዥ ምንድነው? የመንግሥት ግዥ ስለሚመራባቸው ሕጐች፣ ስለዓለም አቀፍ ግዴታዎች፣ ስለመንግሥት ግዥ መርሆዎች፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ በመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ሊኖር ስለሚገባ ሥነ ምግባር፣ ስለ ግዥ ዕቅድና ዑደት፣ ስለግዥ ዓይነቶች፣ ስለ ጨረታ፣ ስለ ግዥ ዘዴዎች፣ ስለ ቴክኒክ ፍላጐት መግለጫ አዘገጃጀት፣ ስለ መደበኛ ጨረታ ሰነድ ይዘትና አጠቃቀም፣ ስለ ጨረታ ግምገማ፣ ስለ ቅድመ ብቃት ማረጋገጫ ጨረታ እና ሰለ አገልግሎት ግዥ በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከየመ/ቤቱ የተውጣጡ ሰልጣኞች በቆይታቸው ሥልጠናው ጥሩ አቅም እንደፈጠረላቸውና የነበረባቸውን ክፍተት ለመሙላትና ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በየመ/ቤታቸው ወደ ተግባር ለመለወጥ አጋዥ እንደሚሆንላቸውም ገልጸዋል፡፡

ለአምስት ቀናት በቆየው የመንግሥት ግዥ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

 

 

9ኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን ተከበረ


የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ከመንግሥት የግዥና የንብረት ማስወገድ አግልግሎት እና ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ባላአደራ ቦርድ ጋር በመተባበር የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀንን ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር  አዳራሽ በድምቀት አከበረ፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሀጂ ኢብሳ እንደተናገሩት “በሕገ መንግሥታችን  የደመቀ ኢትዮጵያዊነታችን  ለህዳሴያችን” የበዓሉ  መሪ ቃል መሆኑን ገልጸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ የህዝቦቿን ጥቅም የሚያረጋግጥ ህg መንግስታዊ ስርዓት ለመመስረት በህዝቦቿ ፈቃድና ፍላጎት ህገ መንግስት አፅድቃ መንቀሳቀስ ከጀመረች 20 ዓመታት እንደተቆጠረ፣ህገ መንግስታችን የሁሉም ህጎች የበላይ የሆነ የህግና የፖለቲካ ሰነድ እንደሆነ፣አገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደች አገር እንደሆነች፣የኢትዮጵያ ህዝቦች በታሪካቸው በርካታ ተጋድሎዎችን መፈጸማቸውን፣ከአድዋ የድል ታሪክ ቀጥሎ በአገራችን ትልቅ ትዕንግርት የተሰራው በህገ መንግስቱ መፅደቅና ለዚሁ ምክንያት በሆነው ተጋድሎ መሆኑን በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ገለፃና ማብራሪያ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም ሕገ መንግስት፥ ብዝሀነት፥ ልማት፥ ዲሞክራሲና ብሄራዊ መግባባት፣የህገ መንግስት፥ እሴቶች፥ ባህሪያትና ዓላማዎች፣የተዛቡ ታሪካዊ ገጽታዎች እንዲስተካከሉ የሚያደርግ፣ለመሰረታዊ ቅራኔዎች መልስ የሚሰጥ ፣የህግ የበላይነትና የልማት ትስስር የሚቀበል ህገ መንግስት፣በህዝቦች መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ፣ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ፣ እና ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ መገንባት በሚሉ ሃሳቦች ላይ   ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በተከበረው የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የመንግሥት የግዥና የንብረት ማስወገድ አግልግሎት እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ባላአደራ ቦርድ  መ/ቤቶች የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን ላይ ከ400 በላይ ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ  የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት