The FDRE Public Procurement & Property Administration Agency

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ

News

በአቅራቢነት ስለመመዝገብ

በኤጀንሲያችን ድረ-ገጽ ላይ በአቅራቢነት በቀላሉ ለመመዝገብ እንዲችሉ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአጠቃቀም ማኑዋል (User Guide for Supplier) በቅድሚያ መመልከት እንዳለብዎት አይርሱ፡፡ በመመሪያው መሠረት ምዝገባዎን ያከናውኑ፡፡

የመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ ሠራተኞች የመልካም አሰተሳሰብ መጀመርያ የሆነውን አካባቢን የማጽዳት ተግባር አካሄዱ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሰራተኞች የመልካም አሰተሳሰብ መጀመርያ የሆነውን አካባቢን የማጽዳት ተግባር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያከናውነው የሚገባውን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን አካባቢን የማጽዳት ዘመቻን በመደገፍ ግንቦት 9/2011 የኤጀንሲውን ቅጥር ግቢ በማጽዳት ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ግንባር ቀደም በመሆን፣ ሠራተኛውን በማበረታታ እና አብረው ቆሻሻን በማጽዳት ተግባር ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡የተለያዩ የኤጀንሲው ዳይሬክቶሬቶች ዳይሬክተሮችና የኤጀንሲው ሠራተኞች ቆሻሻን በማጽዳትና መተላለፊያ መንገዶችን ዘግተው የተቀመጡ ነገሮችን በማንሳት አካባቢው ለእይታ እንዲመችና ጽዱ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም የመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ “አካባቢን ከቆሻሻ ውስጣችንን ከቂምና ከጥላቻ እናጽዳ” ከሚለው መርህ በመነሳት ይህ የጽዳት ዘመቻ ቆሻሻን ብቻ ሳይሆን አእምሮአችንን ለማጽዳት አመላካችና ጥሩ ምሳሌ መሆኑን እንዲሁም ውብና የበለጸገች ከተማን ተባብረን መፍጠር እንዳለብን መልዕክት አሰተላልፈዋል፡፡

በፌ.መ.ግ.ን.አ.የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለተመረጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በግዥና ንብረት አሰተዳደር፣ በመንግስት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ ከሚያዚያ 10-12/2011 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ግዥ ውስን የሆነውን የመንግስት ሃብት ለሁሉም ዜጎች በተቻለ መጠን ዕኩል ሊከፋፈል የሚችልበትን ሥርዓት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ ከአገራዊ በጀት ከ65-70% ግዥ ላይ የሚውለውን የመንግስት በጀት አብዛኛው ሊጠቀም የሚችልበትንና ለሁሉም ዕኩል ዕድል የሚሰጠውን ግልፅ የጨረታ ዘዴ በመጠቀም ለዜጎች ዕኩል የማወዳደር ዕድል ስንሰጥ መሆኑን በሚገባ ገልጸዋል፡፡ወ/ሮ መቅደስ ብርሃኑ በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ ስለ መንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ ግዥ ምንድነው? ዓላማውስ? ግዥ እንዴትና ለምን ይታቀዳል? ስለ ግዥ መረጣ ዘዴ፣ ሰለጨረታ ግምገማ፣ ስለዋጋ ማስተካካያ እንዲሁም የመንግስት ግዥ ዋና ዓላማው ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘት (Value for Money) መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በመቀጠልም አሰልጣኟ ስለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ፣ በአፈጻጸም የታዩ የአሰራር ችግሮች፣ አቅራቢዎች ስለሚያቀርቡት ቅሬታ፣መ/ቤቶች ስለሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት፣ ስለአቤቱታ ማጣራት ሥነ-ሥርዓት፣ስለ ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ እና ስለ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ በዝርዝር ገልጸዋል፡፡አቶ ደበበ ማሞ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የንብረት አስተዳደር ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት በመንግስት ንብረት አስተዳደር ዙሪያ እና ሚና ስላላቸው አካላት፣ስለመንግስት ተሽከርካሪዎች ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም፣ ስለመንግስት ንብረት አወጋገድ፣ ለመንግስት ንብረት አስተዳደር ዓላማ፣ ስለ ንብረት ማስወገጃ ዘዴዎች፣ስለንብረት አሰተዳደር የስራ ተግባርና ሃላፊነት፣ ስለንብረት መለያ ቁጥር እና ስለ ቋሚ ንብረት የእርጅና ቅናሽን በሚመለከት ሥለጠና ሰጥተዋለ፡፡አቶ ዘለቀ ታፈሰ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ስለግዥና ንብረት ኦዲት ሂደቶች፣ኮምፒሊያንስ እና ፕርፎርማንስ ኦዲት፣ ሰለኦዲት ዕቅድ አዘገጃጀት፣ ስለ ኦዲት ስምምነት፣ በግዥና ንብረት ፈጻሚ መ/ቤቶች በኦዲት ወቅት ስለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣ በመ/ቤቶች ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት ስላለው የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ቀናት በቆየው ሥልጠና ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፣ በርካታ ጥያቄዎችም ተነስተው ለጥያቄዎቹም በኤጀንሲው አመራሮች እና በአሰልጣኞቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ ከመጋቢት 26-28/2011 ዓ.ም በዓዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመሰብሰቢያ አደራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር በሥልጠናው ላይ እንደተናገሩት ግዥ ማለት የመንግስትንና የህዝብን ሀብት ለዜጎች ዕኩል የምናካፍልበትና ዕኩል የመግዛትና የመሸጥ ዕድል፣ ዕኩል የማወዳደር ዕድል ስንሰጥ መሆኑን በሚገባ በመግለፅ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች የተዘጋጀዉን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በይፋ በመክፈት ስልጠናዉን አስጀምረዋል፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደግሞ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ከመቅረፍ አንጻር ኤጀንሲው ካቀዳቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች መካከል አንዱ በግዥና ንብረት አስተዳደር ፈጻሚ አካላትን አቅም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከስራ ባህሪያቸው በመነሳት በተለይም ለዩንቨርሲቲዎች በላይ አመራሩ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ያለበትን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረው ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡በኤጀንሲው የሚገኙ አሰልጣኞች ሥልጠናውን ሲሰጡ ስለ ግዥ ዓይነቶች፣ ስለመንግስት ግዥ መርሆዎች፣ስለ ግዥ ዕቅድ ዝግጅትና አስፈላጊነት፣ ስለ ዋጋ ማቅረቢያ፣ ስለጨረታ ግምገማ ሂደቶች እና ስለዋጋ ማስተካከያ፣ በግዥ ፈጸሚ መ/ቤቶች ስለሚካሄዱ የአቤቱታ ማጣራት ሂደት፣ አቤቱታ ስለሚቀርብባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣ ስለጥፋተኝነት ሪፖርት አቀራረብ፣ስለንብረት አስተዳደር የስራ ክፍል ተግባርና ኃላፊነት ስለመንግስት ንብረት አስተዳደር ተግባራት፣ስለንብረት አወጋገድና ስለማስወገጃው አይነቶች በዝርዝርአስረድተዋል፡፡በዚህ ሶስት ቀናት በቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ከ220 በላይ ከተለያዩ የአገራችን የዩንቨርሲቲ አመራሮች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ለተነሱት ጥያቄዎችም በኤጀንሲው አመራሮች እና በአሰልጣኞች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡


በኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለዩኒቨርሲቲዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለዩኒቨርሲቲዎች ከመጋቢት 23-25 /2011 ዓ.ም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የስልጠናው ዋና አላማ ታላላቅ ግዥ ፈጻሚ ዩኒቨርሲቲዎች እና የክልል የግዥ ተቋማት ጋር በቅርበት አብሮ በመስራት የመንግስት ግዥ ግልፅነት የተላበሰ፣ቀልጣፋ፣ወጪ ቆጣቢ፣ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ተመጣጣኝ ገንዘብ እንዲያስገኝ፣ ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡በመቀጠል የመንግሰት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድና አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነጋሽ ቦንኬ ስለመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ የመንግስት ግዥ ስለሚመራባቸው የህግ ማዕቀፎች፣ ስለመንግስት ግዥ ዓላማና መርሆች፣ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ሊኖር ስለሚገባ ተግባር እና ኃላፊነት፣ የአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ እና በአፈጻጸም የታዩ የአሰራር ችግሮች አጠቃላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡በመቀጠልም የመንግሰት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘለቀ ታፈሰ ግዢና ንብረት ኦዲት ሂደትና አጠቃላይ ገፅታዎች፣ ስለግዢና ንብረት ኦዲት ትርጉም፣ ስለግዥና ንብርት ኦዲት አላማዎች፣ ኦዲት ተደርገው ስለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡በመጫረሻም ወ/ሮ መቅደስ ብርሃኑ  ስለመንግስት ተሽከርካዎች ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም፣ ስለመንግስት ንብረት አወጋገድ ሂደት ላይ አጠቃላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ክቡር አቶ ጆንሴ ገደፋ የፌዴራልመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በስልጠናው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህ ስልጠና የታለመለትን አላማ ግብ እንዲመታ ሁሉም የተቋማት አመራሮች ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን ኤጀንሲውም መንግስት የጣላበትን ኃለፊነት በእጅጉ ለመወጣት በቆራጥነት የሚሰራ መሆኑ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡የስልጠናውተሳታፊዎችም በርካታ ሃሳቦችን እና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ በአጀንሲው አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶ ለሶስተ ቀናት የቆየው ስልጠና ተጠናቋል፡፡