The FDRE Public Procurement & Property Administration Agency

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ

Message of the Heads of the Agency

የዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በሁሉም ግዥ ፈጻሚ የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግሥት ግዥ አፈፃፀም እና ንብረት አወጋገድ ረገድ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በመገንባት፣ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ በጥናት ላይ በመመርኮዝ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የአሰራር ማነቆዎችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደርን ለማስፈን እየሰራ ይገኛል፡፡

በመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የአሰራር ማነቆዎችን ለማስወገድ በየበጀት ዓመቱ ለመንግስት ግዥ የሚመደበው ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ንዋይ ተመጣጣኝ የሆነ ፋይዳ (Value for Money) እንዲያስገኝ ከማድረግም በዘለለ በከፍተኛ ወጪ የተገዛው ንብረት ከብክነት በጸዳ መንገድ ሥራ ላይ የሚውልበትን የአሰራር ሥርዓት በማጠናከር እንደ አገር በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ የታለሙ የቀጣይ 10 ዓመት መሪ ዕቅዶችን ግብ ለማሳካት እና ሁለተናዊና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ኤጀንሲው የትኩረት አቅጣጫው በማድረግ በትጋት  የሚሰራ መሆኑን እየገልጽኩ፤ ለዚህ እቅድ መሳካት ሥራዎችን በቅንጅትና በህብረት መስራት ወሳኝ በመሆኑ ኤጀንሲው የሚመለከታቸው የመንግስትና የግል ባለድርሻ አካላት በተለይ የሁሉም ግዥ ፈጻሚ የፌደራል መንግስት መ/ቤቶች አመራርና ፈጻሚዎች ዘርፉ አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግብና በላቀ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቀባችሁና ሚና እንድትወጡ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ ለዚህም መሳካት ኤጀንሲው ያለሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግ ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡

ክቡር አቶ ሀጂ ኢብሳ ገንዶ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር

የምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት

የመንግስት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ተግባራት ከፌደራል መንግስት ዓመታዊ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወሰድ ጥናቶች የሚያመለክቱ ሲሆን ይህ ከፍተኛ የመንግስት ሃብት ቁጠባንና ቅልጥፍናን በተላበሰ መልኩ ያለብክነት ስራ ላይ እንዲውል የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደርን በመርህ ማከናወን የግድ ነው፡፡ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዋነኛ መርህ ደግሞ በግዥ አፈጻጸም ረገድ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ተመጣጣኝ ፋይዳ ወይም ጥቅም ማስገኘት እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 5 ላይ ተገልጿል፡፡

በዚሁ መሰረት ኤጀንሲው ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ እንዲሁም ፍትሐዊ፣ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል በአማካሪ በተከናወነ ጥናት መነሻነት የግዥና ንብረት አስተዳደር ሥራዎች በዘርፉ በሰለጠኑ ሙያተኖች እንዲመራ የሚያስችል የኃላፊዎች እና ባለሙያዎችን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ በBasic, Essential እና Advanced ደረጃዎች የፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠና በመስጠት የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም የመገንባት ሥራዎችን እያከናወነ ያለ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ግዥ ፈጻሚ መ/ቤቶች የግዥ አፈጻጸማቸውን የሚመዝኑበት ቁልፍ የግዥ አፈጻጸም መለኪያዎችን በማዘጋጀትና ክትትል የማድረግ ሥራ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር የህግ ማዕቀፍ የማሻሻል፣ በግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ ረገድ ከግሉ ዘርፍ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የማጣራት እና ውሳኔ አሰጣጥን ግልጽ እና ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ፣ የግዥና ንብረት ኦዲትና ቁጥጥር ሥራዎችን የማጠናከር፣ ዘመናዊ እና በኤሌክትሮኒክ የተደገፈ የመንግስት ግዥ ሥርዓት እንዲኖር የማድረግ፣ የከፍተኛ የሃብት ብክነት የሚታይበትን የመንግስት ተሽከርካሪ አጠቃቀምና ቁጥጥርን ሊያግዝ የሚችል fleet Management System የማበልጸግ እና ሌሎች በርካታ የሪፎርም እና ማሻሻያ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

ስለሆነም በዘርፉ ለሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት እነዚህን የሪፎርም እና ማሻሻያ ሥራዎችን በማጠናከርና፣ሥርዓቱን የበለጠ ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ከዓለም ዓቀፍ መመዘኛዎች አንጻር ተቀባይነት ያለውና ከበርካታ አገራት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ የመንግስት ግዥና ንብረት አስዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ኤጀንሲው የበለጠ ጠንክሮ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ ተገልጋዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተከናወነ ለሚገኘው የማሻሻያ ሥራ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ጥሪ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

ክቡር አቶ ወልደአብ ደምሴ የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር