The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

የፌደራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው ኤጀንሲው ሠራተኞች በሙስና ወንጀል ጥቆማ አቀባበል፤ የአያያዝ ሥርዓትና የማጣራት ስራን በተመለከተ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡
የስብሰባው አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ መንገሻ በመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የሥነ—ምግባር ከፍተኛ ባለሙያ በመግቢያው ላይ እንደተናገሩት  የሥልጠናው ዓላማ ሙስናንና ሥነ-ምግባርን በሚመለከት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሲሆን፤ በአገራችን ግዥ ከፍተኛውን የመንግሥት በጀት ስለሚይዝና ውስብስብም በመሆኑ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው፡፡ ለዚህም በአዋጅ ቁጥር 649/2001 ሥልጣን በተሰጠው መሠረት የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አሰራርን ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን፤ ለቁጥጥርም እንዲያመች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመስጠት የሚተጋ ተቋም መሆኑን ገልጸው ተሳታፊዎች በጥሞና እንዲከታተሉ በማሳሰብ  ስልጠናውን አስጀምረዋል፡፡
አቶ ደረጀ ምትኬ በፌዴራል የሥነ—ምግባርና ፀረ—ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ የችሎት ዐቃቤ ህግ ሥልጠናውን  የሰጡ ሲሆን፤ በሥልጠናውም ሙስና የአንድ አገርን ዕድገት የሚያቀጭጭ፤ ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት የሚሆን ይልቁንም ዜጎች በየተቋማቱ ሊያገኟቸው የሚገቡ የመንግስት አገልግሎቶች በሙስና ሊጎተትና ሊለወጥ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ዕውን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም ስለ ፌደራል የሥነ—ምግባርና ፀረ—ሙስና ኮሚሽን መሠረታዊ ዓላማዎች፤ ኮሚሽኑ ጥቆማ የሚቀበልበት የህግ ማዕቀፍና  በሥልጣን ክልሉ የሚወድቁ ጉዳዮች፤ ኮሚሽኑ ጥቆማ የሚቀበልበት ሥርዓት፤ ለኮሚሽኑ የቀረበው ጥቆማ   ስለሚጠናቀርበትና ለውሳኔ ስለሚቀርብበት ሁኔታ፤ የመረጃ ገምጋሚና ወሳኝ ኮሚቴ ሥልጣንና ተግባር፤ ለኮሚሽኑ የቀረበው ጥቆማ ስለሚያዝበት ሥርዓት፤ የጠቋሚዎች መብት:-የተወሰነን ውሳኔ የመጠየቅ መብትና ቅሬታ የማቅረብ መብት፤ከኃላፊነት ነፃ ስለመሆንና የጠቋሚዎች ጥበቃ ምን ይመስላል? በሚል ገለፃ አድርገዋል፡፡


ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኤጀንሲው ከፌዴራል የሥነ—ምግባርና ፀረ—ሙስና ኮሚሽን ጋር በመሆን በሙስናና ስነ-ምግባር ላይ የተሰጠው ሥልጠና ጥሩ ትምህርት እንዳገኙና በቀጣይም ለስራቸው ጥሩ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡
በቀረበው ገለፃና ማብራሪያ ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የዕለቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ ተጠናቋል፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የሙስና ወንጀል ጥቆማ አቀባበል፤ የአያያዝ ሥርዓትና የማጣራት ስራን በተመለከተ ከ100 በላይ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡              
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት