The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በመንግስት ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግስት ቋሚ ንብረት አስተዳደር  እና በስቶክ አስተዳደር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ሥልጠና ለሚመለከታቸው የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከየካቲት 9-13 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰጠ፡፡
የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደበበ ማሞ እና የጥናትና መረጃ ትንተና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደምሱ አብዲ፣እና የዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች ደረጀ ኃ/ማሪያም እና ወ/ሮ አያልነሽ ዓለሙ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዓላማ ውጤታማና ዘመነዘዊ የስቶክ አስተዳደር መርህንና ሥርዓትን እንዲረዱ፣የስቶክ አስተዳደር ተግባራትን የማከናወን አቅም ለማዳበር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የንብረት አስተዳደር እና የስቶክ አስተዳደር ህግጋትንና ሥርዓትን ጠንቅቀው እንዲያወቁ ግንዛቤ ለመስጠት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኞቹ አጠቃላይ ስያሜን፣ስቶክ መለየትና መመደብን፣መቀበል እና መፈተሽን፣ወጪ ማድረግን ፣የስቶክ መዛግብት የሂሳብ ሥርዓትና ሪፖርትን፣ስቶክ ቆጠራና ቁጥጥርን፣ክምችትን፣ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦችና መርሆዎችን፣በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ቋሚ ንብረቶች የአስተዳደር መዋቅር፣የመጀመሪያ አጠቃላይ ቆጠራ እንቅስቃሴና የመዝገብ ዝግጅት ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ስለቋሚ ንብረት አወጋገድ፣ሪፖርት ስለማቅረብ፣ለቋሚ ንብረት ዋጋ ስለመመደብ፣የቋሚ ንብረቶች መዛግብት አያያዝ ሂደት፣የቋሚ ንብረቶች ዋጋ በሂሳብ እንዴት እንደሚያዝ፣የቋሚ ንብረቶች የዕርጅና ቅናሽ፣ሌሎች ጉዳዮች እና የአቤቱታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት በሚሉ ርዕሶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሰልጣኞች በበኩላቸው በቆይታቸው ከስልጠናው ብዙ ትምህርት እንዳገኙ፣ጥሩ አቅም እንደፈጠረላቸው፣እንዲሁም የነበረባቸውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላትና ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በየመ/ቤታቸው ሲመለሱ ወደ ተግባር ለመለወጥ አጋዥ እንደሚሆንላቸውም ገልፀዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች የቡድን ስራ የተሰራ ሲሆን ስቶክን ምን ያህል ጊዜ ነው መያዝ የሚቻለው? ስቶክ ተይዘው የተመረቱባቸው ጊዜ (Expiry Date) ቢያልፍስ? እስቴፕለር እና ፍላሽ የመሳሰሉት ዋጋቸው ከ1000 ብር በታች እና የአገልግሎት ዘመናቸው ከ1 ዓመት በታች ሆነው እንዴት እንደ ቋሚ እቃ ተይዘው  ሰራተኛች ሲጠፋባቸው አንዲከፍሉ ይደረጋል? አገልግሎታቸውን የጨረሱ እቃዎች በሞዴል 19 ገቢ ይደረጋሉ ወይ ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይም አሰልጣኞቹ የመንግስት ንብረት አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ስልጠናው መዘጋጀቱንና ሰልጣኞች ወደየ መ/ቤታቸው ሲመለሱ ስራ ላይ እንዲያውሉት በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
ለ5 ቀናት በቆየው የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግስት ቋሚ ንብረት አስተዳደር እና በስቶክ አስተዳደር ስልጠና ላይ 200 የሚሆኑ ኃላፊዎችና ባለሙዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡