The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ግዥና የንብረት አስተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት የጋራ ምክክር መድረክ ተካሄደ

በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት መካከል የሚደረገው 6ኛ ዙር የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አዳራሽ ታህሳስ 20 ቀን 2007 ዓም .ተካሄደ፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገራችን በተጨባጭ እየታየ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቀጣይነት ለማረጋገጥ በመንግሰት ግዥ አፈፃፀም እና በንብረት አስተዳደር ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመከላከል እንዲሁም ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሰራርና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በየበኩላችን የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከምንጊዜውም በበለጠ ተቀንጅቶ መስራት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡
በጋራ ተመካክሮ መስራቱ ከመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ የአፈፃፀም ችግሮች የጋራ የሆነ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል ስልት ከመሆኑም ባሻገር በአገር ደረጃ የተጣጣመና በኔት ወርክ የተሳሰረ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቶችን ለመዘርጋትና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀው የጋራ የውይይት መድረኩ በዘርፉ ዙሪያ ችግር ፈቺ የሆነ ሙያዊ ውይይት ለማድረግ እንደሚረዳ አስታውቀዋል፡፡፡፡
በፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመ/ግ/ን/ኦ/ክትትልዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደለ ነጋሽ በበኩላቸው ስለ አራቱ ውጤት አመልካቾች፣ ስለ ሰባቱ አፈፃፀምን ትኩረት ስለአደረጉ አመልካቾች እና ታሪካዊ ዳራቸው ላይ  ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም የቤንሻንጉል ጉ/ብ/ክ/መንግስት የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ገለታ በበኩላቸው የክልሉን ዳራ፣አደረጃጀት፣የአገልግሎቱ  ዋና  ዋና  ተግባርና  ኃላፊነት፣ የግዥና ዉል አስተዳደር ዋና የሥራ  ሂደት፣ በ 2006ዓ.ም በግዥ ዋና የሥራ ሂደት የተከናወኑ ተግባራት፣ በ 2006 ዓ.ም በማስወገድ ዋና የሥራ ሂደት የተከናወኑ ተግባራት ፣በሥራ ላይ ያገጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ መፍትሔዎች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት መካከል በተደረገው 6ኛ ዙር የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ ላይ ከ100 በላይ ተሳታፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት