The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የኤጀንሲው እና የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የምክክር መድረክ ተካሄደ

በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በክልልና የከተማ አስተዳደር የገ/ኢ/ል/ቢሮዎች መካከል የሚደረገው 6ኛ ዙር የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ በሂልተን ሆቴል አዳራሽ ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓም .ተካሄደ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት መንግስት ለሚያንቀሳቅሰው  ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ማስፈፀሚያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኘው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከተሰማሩ ዜጎችና ኩባንያዎች በግብርና በቀረጥ መልክ ከሚሰበሰበው ገንዘብ መሆኑን በመጥቀስ፤ትልቁን ድርሻ የሚይዙት የንግዱ ህብረተሰብ በማለት የምንጠራው አምራቹ፣አከፋፋዩ፣በግንባታ፣በምክር አገልግሎት እና ሌሎች፣በፋይናስና በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩ አካላትና ዜጎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የመንግስት ሀብት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ መንግስት በሥርዓቱ ላይ በየጊዜው ማሻሻያዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ የሀገር ውስጥ አምራችና አቅራቢዎች ከውጭ አገር ተጫራቾች ጋር ሲወዳደሩ ልዩ አስተያየት ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱ አንዱ ማሳያ መንገድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በበኩላቸው ቀደም ሲል አያሌ ምክክሮች በጋራ ተደርገው ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት መደረጋቸውን ገልጸው በዚህ 6ኛ ዙር የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ፣የአይቲ ዘርፍ፣የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ አባላትን ችግር በግዥ ህጉ እንዲሁም የህጉ አፈጻጸም ያስከተለውን ችግር በሰከነ መንፈስ ተወያይቶ ችግሮቹ ላይ እና መፍትሄዎቹንም በተመለከተ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመንግስት እና የግል ዘርፍ የምክክር መድረክ ጽ/ቤት ከፍተኛ አማካሪ አቶ ፍቃዱ ጴጥሮስ የመንግስት ግዥ መሰረታዊ ዓላማና መርሆዎች የመንግስት ግዥ ሥርዓትና የህግ ማዕቀፍ እና በመንግስት ግዥ የአሰራር ሂደት የብረታብረት፣የአይቲ፣የጨርቃጨርቅ እና የኮንስትራክሽን ዘርፎች የሚያጋጥማቸው ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡

በቀረበው ፅሁፍ ላይ አጠቃላይ ውይይት ተደርጎ በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸው፡፡

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፀጋዬ አበበ በማጠቃለያ ሀሳባቸው  ጥናቱ የአንድ ወገን ችግር ብቻ የያዘና በነጋዴዎችም  ላይ የሚታዩ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በመግለፅ የተሰጡት ሃሳቦች እንደግብኣት የሚያዙ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በክልልና የከተማ አስተዳደር የገ/ኢ/ል/ቢሮዎች የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ ላይ ከ180 በላይ ተሳታፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት