The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በመንግስት ቋሚ ንብረት እና ስቶክ አስተዳደር ላይ ሥልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግስት ቋሚ ንብረት አስተዳደር  እና በስቶክ አስተዳደር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ሥልጠና ለሚመለከታቸው የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከታህሳስ 6-10 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰጠ ፡፡
የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደበበ ማሞ እና የጥናትና መረጃ ትንተና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደምሱ አብዲ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዓላማ ውጤታማና የስቶክ አስተዳደር መርህንና ሥርዓትን እንዲረዱ፣የስቶክ አስተዳደር ተግባራትን የማከናወን አቅም ለማዳበር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የንብረት አስተዳደር እና የስቶክ አስተዳደር ህግጋትንና ሥርዓትን ጠንቅቀው እንዲያወቁ ግንዛቤ ለመስጠት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኞቹ አጠቃላይ ስያሜን፣ስቶክ መለየትና መመደብን፣መቀበል እና መፈተሽን፣ወጪ ማድረግን ፣የስቶክ መዛግብት የሂሳብ ሪፖርትን፣ስቶክ ቆጠራና ቁጥጥርን፣ክምችትን፣ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦችና መርሆዎችን፣በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ቋሚ ንብረቶች የአስተዳደር መዋቅር፣የመጀመሪያ አጠቃላይ ቆጠራ እንቅስቃሴና የመዝገብ ዝግጅት ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ስለቋሚ ንብረት አወጋገድ፣ሪፖርት ስለማቅረብ፣ለቋሚንብረት ዋጋ ስለመመደብ፣የቋሚ ንብረቶች መዛግብት አያያዝ ሂደት፣የቋሚ ንብረቶች ዋጋ በሂሳብ እንዴት እንደሚያዝ፣የቋሚ ንብረቶች የዕርጅና ቅናሽ፣ሌሎች ጉዳዮች እና የአቤቱታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት በሚሉ ርዕሶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቆይታቸው ከስልጠናው ብዙ ትምህርት እንዳገኙ፣ጥሩ አቅም እንደፈጠረላቸው፣እንዲሁም የነበረባቸውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላትና ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በየመ/ቤታቸው ወደ ተግባር ለመለወጥ አጋዥ እንደሚሆንላቸውም ገልፀዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች የቡድን ስራ የተሰራ ሲሆን የቋሚ አላቂዎች በዩሲ ላይ ይመዘገባሉ ወይ ? የመኪና የመለዋወጫ ዕቃ ሲመለስ በጣም የተጨመላለቁ በመሆናቸው በቀላሉ ቆጥረን የምንረከባቸው አይደሉም አንድ አይነት መፍትሄ ቢሰጠው፣እኛ አገር በእርጅና የሚወገድ መኪና አለ ወይ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይም አሰልጣኞቹ የመንግስት ንብረት አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ስልጠናው መዘጋጀቱንና ሰልጣኞች ወደየ መ/ቤታቸው ሲመለሱ ስራ ላይ እንዲያውሉት በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
ለ5 ቀናት በቆየው የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግስት ቋሚ ንብረት አስተዳደር እና በስቶክ አስተዳደር ስልጠና ላይ ከ150 በላይ ኃላፊዎችና ባለሙዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት