The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በግዥና ንብረት አሰተዳደር አዋጅ ማሻሻያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ማሻሻያ ዙሪያ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ የሆኑት አቶ ነጋሽ ቦንኬ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ ስለአዋጁ ማሻሻያ ዋና ዋና ዓላማዎች፣ በአዋጁ የተካተቱት ዋና ዋና የማሻሻያ ለውጦች እና ማሻሻያውን ማድረግ  ያስፈለገባቸው ምክንያቶች እንዲሁም ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያያዙ ስለተካተቱ አሰራሮች ላይ ገለጻ አድርጓል፡፡

በመቀጠልም አማካሪው በአፈጻጸም ሲያጋጥሙ የነበሩ እና   ለመልካም    አስተዳደር   ችግር ምክንያት የሆኑ    የአሰራር ጉድለቶች ስለማረም፣ የመንግስት የልማት  ድርጅቶች የመንግስት ግዥና   ንብረት     አስተዳደር ወጥ በሆነ    መንገድ የሚመራበትን ስልት ስለመቀየስ፣ የሀገር ውስጥ ተወዳዳሪዎችን ተሳትፎ የማበረታት ስልት፣ አዋጁን የተሟላ የሚያደርጉ ተጨማሪ ድንጋጌዎችን ስለማካተት የአዋጁን አወቃቀር በማስተካከል ለአፈጸጸም በይበልጥ አመቺ ስለማድረግ፣ በግዥ ሂደት የሚነሱ አቤቱታዎችን ማጣራት እና  ውሳኔ አሰጣጥ    ሂደትን ገለልተኛ እና ተዓማኒነት እንዲኖረው ስለማስቻል፣ እንዲሁም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ   ግዢ ሥርዓትን    በአዋጁ በማካተት ዘመናዊ የንብረት    አስተዳደር  ሥርዓትን እንዲኖር ማድረግ በሚል በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡በመጨረሻም አቶ ወልደአብ ደምሴ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በማጠቃለያው ንግግር ላይ እንደተናገሩት ግዥ ማሳለጫ እንጂ ማደናቀፊያ መሆን እንደሌለበት፣ ግዥን ዘመናዊ በማድረግ የስጋት ተጋላጭነትን መቀነስ፣ በCheck and Balance አመኔታን ማሳደግ እና የሰው ንኪኪን በመቀነስ ግልጽነት ያለው አሰራር መስራት መሆኑን ገልጸው፣ የመንግስት አጠቃላይ ዓላማው ሕዝቡ ግዥ ላይ አመኔታን እንዲያገኝ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በቆየው በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር አዋጅ ማሻሻያ ዙሪያ ውይይት ላይ የሚመለከታቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች የበላይ ሃላፊዎችና የግዥ ስራ ክፍል ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት