The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት እና ከኦዲት ቦርድ ሠራተኞች ጋር በመሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ የፀረ-ሙስናን ቀን ህዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒሰቴር የስብሰባ አዳራሽ አከበረ፡፡

አቶ ይልማ ዘውዴ በገንዘብ ሚኒሰቴር የስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በህልውናችን ላይ የተጋረጠውን ሙስናን በመግታት እድገታችንን  ለማፋጠን እንረባረብ የሚለውን በንባብ ካሰሙ በኋላ፣ ስለሙስና ትርጉምና መገለጫዎቹ፤ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር ስለሚዳርጉ መንስኤዎች፤ የሙስና ዓለም አቀፍዊ  ሁኔታው  በኢትዮጵያ ላይ ስለአሳረፈው ተጽዕኖ፤ ስለሀገራዊ የፀረ ሙስና ትግሉ እንቅስቃሴና የተገኘ ውጤት፣ስለስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ትግሉ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ከበቡሽ ሽፈራው በፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ማሰወገድ አገልግሎት የስነምግባርና የፀረ- ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ባቀረቡት ጽሁፍ ከሙስና ወንጀል ሕጎች ተነስተው ስለወንጀል ምንነት፣ ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት መሟላት ስላለባቸው ሁኔታዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች በመንግሥት ሥራ ላይ ሰለሚፈፅሟቸው ወንጀሎች፣ ሌሎች ሰዎች በመንግሥት ሥራ ላይ ሰለሚፈፅሟቸው ወንጀሎች፣ ሰለዝርዝር የሙስና ወንጀል ድንጋጌዎች፣ በሥልጣን አለአግባብ ስለመገልገል፣  የማይገባ ጥቅም ሰለመቀበል፣ የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን ስለመምራት፣ በሥልጣን ሰለመነገድ፣ ያለአግባብ ጉዳይን ሰለማጓተት፣ ዋጋ ያለውን ነገር ያለክፍያ ወይም ያለበቂ ክፍያ ሰለማግኘት፣በሌለው ሥልጣን ስለመጠቀም ሰፋ ባለ መልኩ አሰረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ከፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በሁለት የኤጀንሲው ሰራተኞች ስለ ሙስና ግጥሞች የተነበቡ ሲሆን ለበዓሉም ድምቀትን ሰጥቶታል፡፡ በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የዕለቱ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የፀረ-ሙስና ቀን በዓል አከባበር ላይ የገንዘብ ሚኒሰቴር እና የተጠሪ መ/ቤቶች ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ.የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት