The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ለተመረጡ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግስት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለተመረጡ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግስት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ ከጥቅምት 6 እስከ ህዳር 30/2012 ዓ.ም. የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡

አቶ ነጋሽ ቦንኬ  የክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አማካሪ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የስልጠናው ዋና ዓላማ የፋይናንስ ዘርፍ የሆነውን የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት እንዲሁም የግዥ ሂደት እና የንብረት አወጋገድ ተግባራት ለዚህ ዓላማ የተዘጋጁ የህግ ማዕቀፎችን በጠበቀ መልኩ ማስኬድ እንዲቻል፣ ይልቁንም የፌድራል ባለበጀት መ/ቤቶችን የመፈጸም አቅም በማሳደግ፣ በዕቅድ ዝግጅትና አፈጻጸም፣ የበጀት አፈጻጸማቸውንና የግዥ አፈጸጸም ግንዛቤን በማሳደግ ለሚሰጡት አሰተዳደራዊ ውሳኔ ተጠያቂነት እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ የአሰራር ሰርዓትን በማስረጽ የህግ የበላይነትን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ የታለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ለተመረጡ የፌዴራል ባለበጀት ተቋማት በተዘጋጀ የግዥ አፈፃፀም እና የንብረት አስተዳደር የአቅም ማሳደጊያ ስልጠና ላይ የተለያዩ አሰልጣኞች ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ ስለመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ የመንግስት ግዥ ስለሚመራባቸው የህግ ማዕቀፎች፣ ስለመንግስት ግዥ ዓላማና መርሆች፣ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ሊኖር ስለሚገባ ተግባር እና ኃላፊነት፣ ስለግዥ አፈጻጸም ሂደት እና ስለውል አስተዳደር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም አሰልጣኞቹ ስለመንግስት ግዥና ንብረት አወጋገድ አቤቱታና የጥፋተኝነት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ፣ በአፈጸጸም ስለታዩ የአሰራር ችግሮች፣ ስለአቤቱታ የአቀራረብ ሥነ-ሥርዓት፣ ሰለ ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ እንዲሁም ስለመንግስት ተሸከርካሪዎቸ ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም እና ስለመንግስት ንብረት አወጋገድ ሂደት፣ ስለ ግዥና ንብረት ኦዲት ሂደቶች የኦዲት ሪፖርቱ ስለሚይዛቸው ዋና ዋና ይዘቶች ስለ መንግስት ግዥና ንበረት ኦዲት እና ክትትል የ2011 ዓ.ም ዕቅድና ክንውን እና በ2011 በጀት ዓመት በኦዲት ወቅት የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች ላይ አጠቃላይ ገለጻ አድርጓል፡፡

በሥልጠናው ላይ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ለአንድ ወር ውሰጥ በአራት ጊዜ ተከፋፍሎ  ለተመረጡ ተቋማት በተሰጠው ሥልጠና ላይ 500 የሚሆኑ በቀጥታ ለሚመለከታቸው ለየተቋማቱ የሥራ ሃላፊዎች፣ የአሰተዳደርና ፋይናንሰ ዳይሬክተር፣ የግዥ ዳይሬክተር፣ የንብረት ዳይሬክተር፣ የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴ አባላትና የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ዳይሬክተር ተሳታፊ ሆነዋል፡፡