The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በግዥ አፈፃፀም ሂደት በሚታዩ ችግሮችና የሙስና ስጋቶች ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ ፈፃሚ መ/ቤቶችና በአቅራቢዎች የሚታዩ የአፈፃፀም ችግሮችና የሙስና ስጋቶችን አስታወቀ

 

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክትር አቶ ፀጋዬ አበበ በግዥ ፈፃሚ መ/ቤቶችና በንግዱ ማህበረሰብ /አቅራቢዎች/ በተደጋጋሚ በሚታዩ ዋና ዋና የአፈፃፀም ችግሮችና የሙስና ስጋቶች ዙሪያ ነሀሴ 6 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትየጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል ፡፡

አቶ ፀጋዬ የመንግስት ግዥና ንብረት የሚመራባቸው የህግ ማዕቀፎችና የአፈፃፀም ሰነዶች፣የመንግስት ግዥ መሰረታዊ መርሆዎች፣ዓላማዎችና ዋና ዋና ተግባራት፣የግዥ ፈፃሚ መ/ቤት ኃላፊነት፣የተፈቀዱ የግዥ ዘዴዎች፣በመንግስት የግዥ የአፈፃፀም ሂደት የሚታዩ ችግሮችና የሙስና ስጋቶች፣የግዥ ችግሮቹን ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎችና በኤጀንሲው በ2007 በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ ዋና ዋና ስራዎች ላይም  ገለፃ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ሌሎች ተጫራቾችን በሚገድብ ወይም አንድን ተጫራች በሚጠቅም መልኩ የቴክኒክ ፍላጎት ዝርዝር ሰፔሲፊኬሽን ማዘጋጀት፣በአንድ ጥቅል ጨረታ መግዛት የሚቻለውን በትንንሽ በርካታ ጨረታዎች በመከፋፈል ግዥ መፈፀምና በጥቃቅን ምክንያት ብቁ አቅራቢዎችን ከጨረታ ውጭ ማድረግ  በግዥ ፈፃሚ መ/ቤቶች ከሚጠቀሱ ከብዙዎቹ በጥቂቱ  የአፈፃፀም ችግሮችና የሙስና ስጋቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በአቅራቢዎች ወይም በንግዱ ማህበረሰብ ተጫራቾች እርስ በርስ በመመሳጠር የተጋነነ የግዥ ዋጋ ማቅረብ፣የተጭበረበረ የብቃትና ልምድ፣የህጋዊነት የጨረታ ወይም የውል ማስከበሪያ ሰነድ ማቅረብ፣ውል ከፈፀሙ በኋላ ተጨማሪ ዋጋ ካልተከፈለኝ በቀድሞ ዋጋ ማቅረብ አልችልም በማለት የዕቃ ወይም የአገልግሎት አቅርቦትን ማቋረጥ የሚጠቀሱ ችግሮችና የሙስና ስጋቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ፀጋዬ ከንግዱ ማህበረሰብ ወኪሎች እንዲሁም በክልልና የከተማ መስተዳድር የመንግስት ግዥና ንብረት የስራ ኃላፊዎች ጋር በሚያጋጥሙ ችግሮች የምክክር መድረክ ማድረግ፣ከመንግስት ግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደር ስራ ጋር ግንኙነት ላላቸው የመ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተከታታይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና መስጠትና… ወዘተ ችግሮችን ለመፍታት

እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በክቡር ደ/ር አብርሃም ተከስተ በገ/ኢ/ል/ሚር በልማት ዕቅድና የኢኮኖሚ አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አወያይነት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር አለማየሁ ጉጆ በገ/ኢ/ል/ሚር የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደርና ቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችንና አሰተያየቶች ተገቢ መሆናቸውን ገልፀው ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተው ግዥ በመንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ መሆኑን በመግለፅና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ መሆኑን ጠቅሰው ትኩረት ሰጥቶ መስራት ጠቃሚ መሆኑን በማሳወቅ በግዥና ንብረት አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን በመንግስት፣በግዥ ፈፃሚ መ/ቤቶችና በአቅራቢዎች እጅ ለእጅ መያያዝ መፈታት ያለበት ዘርፍ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በቆየው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የገ/ኢ/ል/ሚር፣የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ፣ የግዥ ፈፃሚ መ/ቤቶችና የአቅራቢዎች የምክክር መድረክ ላይ ከ135 በላይ   ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

 

 

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት