The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ፕሮጀክት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚተገበረው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (Electronic Government Procurement)ን በሚመለከት ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች ሰኔ 1 እና 2 ቀን 201 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት ፕሮጀክቱን የማስተዋወቅ ሥራ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የኤክትሮኒክ ግዥ ሪፎርም ማለት ከወረቀትና ከተለመደው አሰራር በመውጣት የአገራችን የግዥ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በኮምፒውተር የታገዘ የግዥ ዘዴ ለመፈጸም መሸጋገር መሆኑን አስረድተዋል፡፡በመቀጠልም ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ ይህንን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ፕሮግራም ማካሄድ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የመንግስት ግዥ ሙያ እንደመሆኑ በሙያተኞች መመራት ስላለበት እና በኤጀንሲው ሰራተኞች መካከል ዕኩል የኤክትሮኒክ ግዥን መረጃ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል፣ የኤክትሮኒክ ግዥን የሚተገብሩ ባለቤቶችም የኤጀንሲው ሰራተኞች በመሆናቸው እኩል ግንዛቤ ለመፍጠር የታሰበ በመሆኑን እና የኤጀንሲው ሰራተኞች በሙሉ ለኤሌክትሮኒክ ግዥ ባለድርሻ አካል በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘዉም ኤጀንሲዉ ከሚያካሂዳቸዉ ሪፎርም ስራዎች ዉስጥ የግዥ እና የንብረት ፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠና፣የቁልፍ ግዥ አመልካቾች፣የኤሌክትሮኒክ ግዥ እና አዋጅና መመሪያ መሻሻያ ሥራዎችም እየተሰሩ መሆናቸዉን አክለዉ ገልፀዋል፡፡በዉይይት መድረኩ ላይ የኤጀንሲዉ አመራሮች ስለመንግስት ግዥ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የመንግስት ግዥ ዕድሎች እና ሥጋቶች፣ የኤሌክትሮኒክ ግዥን ከመተግበር የሚገኙ ዋና ዋና ጥቅሞች ዉስጥ የመንግስትን ግዥ ስርዓትና አሰራር ግልፀኝነትን ማሳደግ፣በግዥ ሂዳት ዉስጥ ጊዜን በማሳጠር ጥራትን ማሻሻል፣የገንዘብ የመግዛት አቅምን ማሳደግ እንዲሁም በግዥና በሻጭ መካከል ያለዉን መተማመን በማሻሻል ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡በሥልጠናው ላይ ሰራተኛው በቡድን ተከፋፍሎ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣በወይይቱም ላይ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለሁለት ቀን በቆየው የመንግስት የኤክትሮኒክ ግዥ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ኤጀንሲው ሰራተኞች በሙሉ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢፌድሪ የመ.ግ.ን.አ.ኤ.የህዝብ ግንኑነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት