The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለተመረጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በግዥና ንብረት አሰተዳደር፣ በመንግስት ግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ ከሚያዚያ 10-12/2011 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ግዥ ውስን የሆነውን የመንግስት ሃብት ለሁሉም ዜጎች በተቻለ መጠን ዕኩል ሊከፋፈል የሚችልበትን ሥርዓት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ ከአገራዊ በጀት ከ65-70% ግዥ ላይ የሚውለውን የመንግስት በጀት አብዛኛው ሊጠቀም የሚችልበትንና ለሁሉም ዕኩል ዕድል የሚሰጠውን ግልፅ የጨረታ ዘዴ በመጠቀም ለዜጎች ዕኩል የማወዳደር ዕድል ስንሰጥ መሆኑን በሚገባ ገልጸዋል፡፡ወ/ሮ መቅደስ ብርሃኑ በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ ስለ መንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ ግዥ ምንድነው? ዓላማውስ? ግዥ እንዴትና ለምን ይታቀዳል? ስለ ግዥ መረጣ ዘዴ፣ ሰለጨረታ ግምገማ፣ ስለዋጋ ማስተካካያ እንዲሁም የመንግስት ግዥ ዋና ዓላማው ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘት (Value for Money) መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በመቀጠልም አሰልጣኟ ስለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ፣ በአፈጻጸም የታዩ የአሰራር ችግሮች፣ አቅራቢዎች ስለሚያቀርቡት ቅሬታ፣መ/ቤቶች ስለሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት፣ ስለአቤቱታ ማጣራት ሥነ-ሥርዓት፣ስለ ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ እና ስለ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ በዝርዝር ገልጸዋል፡፡አቶ ደበበ ማሞ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የንብረት አስተዳደር ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት በመንግስት ንብረት አስተዳደር ዙሪያ እና ሚና ስላላቸው አካላት፣ስለመንግስት ተሽከርካሪዎች ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም፣ ስለመንግስት ንብረት አወጋገድ፣ ለመንግስት ንብረት አስተዳደር ዓላማ፣ ስለ ንብረት ማስወገጃ ዘዴዎች፣ስለንብረት አሰተዳደር የስራ ተግባርና ሃላፊነት፣ ስለንብረት መለያ ቁጥር እና ስለ ቋሚ ንብረት የእርጅና ቅናሽን በሚመለከት ሥለጠና ሰጥተዋለ፡፡አቶ ዘለቀ ታፈሰ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ስለግዥና ንብረት ኦዲት ሂደቶች፣ኮምፒሊያንስ እና ፕርፎርማንስ ኦዲት፣ ሰለኦዲት ዕቅድ አዘገጃጀት፣ ስለ ኦዲት ስምምነት፣ በግዥና ንብረት ፈጻሚ መ/ቤቶች በኦዲት ወቅት ስለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣ በመ/ቤቶች ውስጥ ትልቅ ሃላፊነት ስላለው የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ቀናት በቆየው ሥልጠና ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፣ በርካታ ጥያቄዎችም ተነስተው ለጥያቄዎቹም በኤጀንሲው አመራሮች እና በአሰልጣኞቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት