The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ዙሪያ ከመጋቢት 26-28/2011 ዓ.ም በዓዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመሰብሰቢያ አደራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አጄንሲ ዋና ዳይሬክተር በሥልጠናው ላይ እንደተናገሩት ግዥ ማለት የመንግስትንና የህዝብን ሀብት ለዜጎች ዕኩል የምናካፍልበትና ዕኩል የመግዛትና የመሸጥ ዕድል፣ ዕኩል የማወዳደር ዕድል ስንሰጥ መሆኑን በሚገባ በመግለፅ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የበላይ አመራሮች የተዘጋጀዉን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በይፋ በመክፈት ስልጠናዉን አስጀምረዋል፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደግሞ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ከመቅረፍ አንጻር ኤጀንሲው ካቀዳቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች መካከል አንዱ በግዥና ንብረት አስተዳደር ፈጻሚ አካላትን አቅም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከስራ ባህሪያቸው በመነሳት በተለይም ለዩንቨርሲቲዎች በላይ አመራሩ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ያለበትን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረው ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡በኤጀንሲው የሚገኙ አሰልጣኞች ሥልጠናውን ሲሰጡ ስለ ግዥ ዓይነቶች፣ ስለመንግስት ግዥ መርሆዎች፣ስለ ግዥ ዕቅድ ዝግጅትና አስፈላጊነት፣ ስለ ዋጋ ማቅረቢያ፣ ስለጨረታ ግምገማ ሂደቶች እና ስለዋጋ ማስተካከያ፣ በግዥ ፈጸሚ መ/ቤቶች ስለሚካሄዱ የአቤቱታ ማጣራት ሂደት፣ አቤቱታ ስለሚቀርብባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣ ስለጥፋተኝነት ሪፖርት አቀራረብ፣ስለንብረት አስተዳደር የስራ ክፍል ተግባርና ኃላፊነት ስለመንግስት ንብረት አስተዳደር ተግባራት፣ስለንብረት አወጋገድና ስለማስወገጃው አይነቶች በዝርዝርአስረድተዋል፡፡በዚህ ሶስት ቀናት በቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ከ220 በላይ ከተለያዩ የአገራችን የዩንቨርሲቲ አመራሮች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ለተነሱት ጥያቄዎችም በኤጀንሲው አመራሮች እና በአሰልጣኞች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡


በኤጀንሲዉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት