The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የ2006 የዕቅድ አፈጻጸምና የ2007 ዕቅድ መርሀ ግብር ላይ ውይይት ተደረገ

የኤጀንሲው ስራዎች ዕቅድ አፈፃፀም በአማካኝ 92% ሲሆን

የፋይናስ አጠቃቀም 91.3%፣ መሆኑ ተገለፀ

 

የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የ2006 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን፣ የ2007 በጀት ዓመት ዕቅድንና ስትራቴጂያዊ የአፈጻጸም ማዕቀፍን በሚመለከት ነሐሴ 2 ቀን 2006 ዓ.ም ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች ጋር በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዓላማ ባለፈው የ2006 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሥራ ምን ይመስላል? በ2007 በጀት ዓመትስ ምን ሊሰራ ታስቧል? በሚለው ላይ ለመወያየት ሲሆን፣ አያይዘውም ሀገራችንን አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ ሁሉም ዜጋ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በመሆኑ ሃገራዊ ዕቅድን ለማሳካት ይህንን መርህ መከተል እንዳለብን አሳስበዋል፡፡

አቶ አድማሱ ማሞ የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በኤጀንሲው የተከናወኑ የ2006 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት በሚመለከት በለውጥ ሠራዊት ግንባታ የ1 ለ5 አደረጃጀትን፣ከሕዝብ ክንፍ ጋር ስለተደረጉ የቋሚ ምክክር መድረኮች፣ ለተለያዩ ፈጻሚ አካላት ስለተሰጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ ለደንበኞችና ተገልጋዮች ስለተሰጡ ሙያዊ ድጋፎች፣ ከፌዴራል የመንግሥት መ/ቤቶች በግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ስለተደረጉ የኦዲትና የክትትል ሥራዎች፣ ተጫራቾች በግዥ ፈጻሚ የመንግሥት መ/ቤቶች ላይ ያቀረባቸው አቤቱታዎችና ግዥ ፈጻሚ የመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ

ባቀረቡአቸው የጥፋተኝነት ሪፖርቶች ላይ ስለተሰጡ ወሳኔዎች፣ስለተቀረጹ የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም፣ በአፈጻጸም ሂደት ስለአጋጠሙ የአሰራር ክፍተቶችና የተወሰዱ ወቅታዊ የማስተካከያ እርምጃዎችን በሚመለከት በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም ኤጀንሲው በ2006 በጀት ዓመት ውስጥ ያከናወናቸውን የዕቅድ አፈጻጸም ከአራቱ እይታዎች አንፃር የተገልጋይ ዕይታ 95%፣ የፋይናንስ ዕይታ 91.3%፣ የውስጥ አሰራር ዕይታ 85%፣ የመማማርና ዕድገት ዕይታ 97%፣ የ4ቱም ዕይታዎች አማካይ 92%መሆኑንም  አስረድተዋል፡፡

አቶ መሥፍን መኮንን የለውጥ ትግበራ ዕቅድ፣ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት በበኩላቸው ስለ ስትራቴጂያዊ የአፈጻጸም ማዕቀፍ ተልዕኮ፣ራዕይና እሴቶች እንዲሁም  ስለ 2007 በጀት ዓመት ግቦች፣ ዒላማዎችና የክትትል ሥልትን በተመለከተ በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርና ም/ዋና ዳይሬክተር የተሰጠው ሪፖርት ጥሩ እንደነበረና በ2007 በጀት ዓመትም ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በቆየው የኤጀንሲው የ2006 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2007 በጀ ዓመት ዕቅድ ውይይት ላይ ከ90 በላይ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት