The FDRE Public Procurement & Property Administration Agency

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ

በግዥና ንብረት ኦዲት ግኝት ዙሪያ ከመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የጋራ ምክክር መድረክ ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በዋና ዋና የኦዲት ግኝቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር  በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ ከመስከረም 7–8/2011 ዓ.ም. የጋራ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የምክክር መድረኩ ዓላማ በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ምክክር በማድረግ የሚፈቱበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንዲያስችል የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በሀገራችን እየተመዘገበ ከሚገኘው ሁለንተናዊ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግስት ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት በየዓመቱ ለመንግስት ግዥ እንደሚመድብና ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስት ገንዘብ የተዘረጋውን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር የህግ ማዕቀፍን ተከትሎ ሥራ ላይ እንዲውልና ውጤታማ እንዲሆን ኤጀንሲው በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣንና ሃላፊነት መሠረት በማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም በመንግስት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ለስራ ኃላፊዎች እና ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት፣ የኮምፕሊያንስ ኦዲት በማድረግ በግኝቶቹ መሰረት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ክትትል በማድረግ ፍትሃዊ፣ ግልጽና ቁጠባን ማዕከል ያደረገ የግዥ እና ንብረት አሰተዳደር ሥርዓት እንዲኖር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ያሉና በዚያው ልክ ቀላል የማይባሉ ለውጦችም እየተመዘገቡ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ዘለቀ ታፈሰ በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በ2010 ዓ.ም በፌዴራል የግዢ እና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት በተደረገ የግዢ ኦዲት ወቅት ስለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣በ2010ዓ.ም በዋና ኦዲተር ኦዲት ወቅት በግዢ፣ በንብረትና በተሸከርካሪ ስምሪት ላይ ስለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣ በ2010ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል የግዢ ኦዲት ተደርገው የኦዲት ግኝት ስለታየባቸው መ/ቤቶችና የግኝቶቻቸው ደጋፊ ሰነዶች፣ በ2011ዓ.ም ኦዲት ወቅት ግኝቶችን በመቀነስ የተሻለ የግዢ፣የንብረትና የተሽከርካሪ ስምሪት አፈፃፀም እንዲኖር የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ስለማድረግ፣ በግዢ፣ በንብረትና በተሽከርካሪ ስምሪት ስርአቱ ውስጥ ያሉ በኦዲቱ የተለዩትን ግኝቶችና በምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሐሳቦችን በማካተት የአቅም ግንባታውን ስራ የበለጠ ተደራሽ ስለማድረግ እና የኦዲት ግኝቶችን በሪፖርት ላይ በተገለፀው ጊዜ እርምት እርምጃ ወስዶ በወቅቱ ያለማሳወቅ ምክንያትን ለመለየትና ለወደፊቱ የመፍትሄ አቅጣጫ ስለማስቀመጥ አስረድተዋል፡፡
አቶ ነጋሽ ቦንኬ በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ስለአቤቱታ ማጣራት፣ አቀራረቡና ስነ-ሥርዓቱ፣ በግዥ ፈጻሚው መ/ቤት ስለሚካሄድ የአቤቱታ ማጣራት ሂደት፣ ስለግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ አቤቱታ ስለሚቀርብባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣አቤቱታ ማቅረብ ስለማይቻልባቸዉ ጉዳዮች፣የጥፋተኝነት ሪፖርት ስለማይቀርብባቸው ሁኔታዎች፣ የጥፋተኝነት ሪፖርት ስለሚቀርብባቸው ጉዳዮች ላይ እና ስለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ እና በአፈጻጸም ስለታዩ የአሰራር ችግሮች፣ በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን አገልግሎቱ ስለፈጸማቸዉ ግዥዎች፣ ስለውል አስተዳደር ተግባራት አፈፃፀም፣ስለአጋጠሙ ችግሮች፣ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር የተuማት ሚና፣በአጠቃላይ በ2010 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና ችግሮችን በመፍታት ረገድ የኤጀንሲው፤ አገልግሎቱና ተጠቃሚ መ/ቤቶች ሚና በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ለጥያቄዎቹም መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለሁለት ቀን በቆየው በዚህ የምክክር መድረክ ስብሰባ ላይ 130 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት