The FDRE Public Procurement & Property Administration Agency

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ

የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤጀንሲ ከክልል አቻ ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከከተማ አስተዳደር የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ተቆጣጣሪ አካላት ጋር በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ነሐሴ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በሀገራችን እየተመዘገበ

ከሚገኘው ሁለንተናዊ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግስት ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት በየዓመቱ ለመንግስት ግዥ እንደሚመድብ፣ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስት ገንዘብ የተዘረጋውን የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር የህግ ማዕቀፍን ተከትሎ ስራ ላይ እንዲውልና ውጤታማ እንዲሆን በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሯ ይህ የጋራ የውይይት መድረክ በሀገር ደረጃ የተናበበ የግዥና ንብረት አሰተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግና በየደረጃው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራን ተጣጥመውና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማድረግ አንጸር በመንግስት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን በአፈጻጸም ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንም ሆነ መልካም ተሞክሮዎች የምንላቸውን ፊት ለፊት በግልጽ በማንሳት ጥልቀት ያለው ውይይት በማድረግ የምናገኘውን መልካም ልምዶች በመቀመር የሥራዎቻችን ልምድ የምንቀስምበት ሁሌም ለተሻለና ለላቀ ውጤት በመትጋት በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ የሆነ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የጸዳ፣ አድሎአዊ አሰራርን የሚነቅፍ፣ በሀገርና በህዝብ ተጠቃሚነት የሚረካ አዕምሮ በማበልጸግ በግዥ ዙሪያ የተጋረጡ አሉታዊ አመለካከቶችን በማረም ለሕዘባችን ተጠቃሚነት ሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

አቶ ፀጋዬ አበበ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አሰተባባሪና የሥልጠና አማካሪ የሆኑት የ2009 ዓ.ም. የቁልፍ የግዥ አመላካቾች /KPI/ አፈጻጸም ሂደትና የወረዳ ኦዲት ሽፋን በአራቱ /በትግራይ፣ደቡብ፣ኦሮሚያና አማራ/ለሙከራ በተመረጡ ክልሎች KPI እንዲተገብሩ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የ2009 ዓ.ም. የቁልፍ የግዥ አመላካቾች /KPI/ አፈጻጸም ሂደትና የወረዳ የግዥ አፈጻጸምን ሂደትና የሸፋን ደረጃ ተሞክሮ እንዲሁም የአማራ ክልል የመንግስት ግዥና ንብረት ማሰወገድ አገልግሎት የ2010 ዓ.ም. አፈጻጸምና የጋጠሙ ተግዳሮቶችን በክልሉ ተወካዮች ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ተነስተው ለጥያቄዎቹም መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው በዚህ የምክክር መድረክ ስብሰባ ላይ 100 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡