The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በአዋጅና መመሪያዎች ማሻሻያ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አሁን በስራ ላይ ባለው እና በተሻሻለው ረቂቅ የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅና መመሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 18-19 ቀን 2006ዓ›ም በኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አደረገ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ረቂቅ ሰነዱ በኤጀንሲው ሁለት የማሻሻያ ቡድኖች እንደተዘጋጀ ገልፀው ያለቀና የደቀቀ ሰነድ ነው ተብሎ እንዳይታሰብ በማሳሰብ ሰነዶቹ በድጋሚ በተሻለ ሁኔታ የሚታዩበት መንገድ እንዳለ በማሳወቅ የውይይቱ ዋና ዓላማ ለአዋጁና ለግዥና ንብረት አስተዳደር መመሪያዎች ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑን በመግለፅ ተሳታፊዎች ውጤታማ የሆነ ውይይት አዳዲስ ሀሳቦች፣ጥያቄዎችና አስተያቶች አንስተው ያነሱዋቸውን ሃሳቦች በድጋሚ በፅሁፍ ለመንግሰት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲልኩ አሳስበዋል፡፡

በፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ኮከብ አሁን በስራ ላይ ባለው እና በተሻሻለው ረቂቅ የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ መካከል ያሉ ልዩነቶችንና የተጨመሩ አዳዲስ ሀሳቦችን በማንሳት ትርጓሜን፣የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር መርሆዎችን፣የምንግስት መ/ቤት የበላይ ኃላፊ ሃላፊነትን፣የግዥና ንብረት አስተዳደር ተግባርና ሀላፊነትን በአጠቃላይ እስከ አዋጁ ምዕራፍ 15 ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ላይ በነባሩና በተጨመሩ አዳዲስ ሀሳቦች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡

በኤጀንሲው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር የግዥ አፈፃፀምና የንብረት አወጋገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወልደአብ ደምሴ በበኩላቸው አሁን በስራ ላይ ባለውና በተሻሻለው ረቂቅ የግዥ መመሪያ መካከል ያሉ ዋና ዋና ልዩነቶች ማለትም የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴ ተግባርና ኃላፊነት፣የተርንኪ ግዥና ትርጓሜው፣ በመንግስት ግዥ አፈፃፀም ላይ የሚቀርብ አቤቱታና ስለ ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ የቦርድ አባላት ስያሜና ዘመን፣ የግዥ ዘዴዎችና አፈፃፀማቸው በአጠቃላይ ከመመሪያው መግቢያ እስከ ክፍል 12 ድረስ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡

በፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ትዕግስት ደበበ በበኩላቸው የፌደራል መንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 9 /2003 ላይ የተደረጉ ዋና ዋና ማሻሻያዎች በትርጋሜ፣መርሆዎች፣የንብረት አስተዳደር ተግባርና ኃላፊነት፣የመንግስት ንብረቶች አስወጋጅ ኮሚቴ አወቃቀርና ተግባርና ኃላፊነት፣የንብረት አስተዳደር እቅድ ስለማዘጋጀትና ዕቅዱ ስለሚፀድቅበትና ስለሚሻሻልበት ሁኔታ በአጠቃላይ ከአንቀፅ 1 እስከ 60 ባሉት አንቀፆች ላይ በነባሩና በተሻሻለው አዳዲስ ሀሳቦች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል::

 

በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ አወያይነት በቀረበው፣አሁን በስራ ላይ ባለውና በተሻሻለው የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅና መመሪያዎች ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ አስተያቶች፣ጥቄዎችና ገንቢ ሃሳቦች ተነስተው ለግንዛቤ ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች በአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም በመዝጊያው ሥነ ሥርዓት ላይ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፀጋዬ አበበ  የሀገሪቱን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል ተሳታፊዎች ላደረጉት አሰተዋፅኦ በማመስገን ለተሰጡት ግብዓቶች  ማሻሻያ ቡድኑ ላይ ተጨማሪ ሰዎችን በማካተት እንደገና እንደሚታይ በማሳወቅ ሚያዚያ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ተሳታፊዎች ለኤጀንሲው የማሻሻያውን የፅሁፍ አስተያየት ጥያቄና ሀሳቦች የሚልኩበት ቀን መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በቆየው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲና ባለድርሻ አካላት ባደረጉት አሁን በስራ ላይ ባለው እና በተሻሻለው ረቂቅ የግዥና ንብረት አስተዳደር መመሪያ ውይይት ላይ  ከ130 በላይ ተሳታፊዎች ውይየቱን ተካፍለዋል፡፡


ከፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ.ሕዝብ ግንኙነት ኮሚዩኒኬሽን  ዳሬክቶሬ