The FDRE Public Procurement & Property Administration Agency

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ

በኤጀንሲው የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድን በሚመለከት ከመላው ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመላው የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር የ2011 የበጀት ዓመት ዕቅድን በተመለከተ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ–ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የስብሰባው ዓላማ በኤጀንሲው በ2011 የበጀት ዓመት በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን የታቀደ ሲሆን፣ ይህ ዕቅድ በትክክል እንዲከናወን ከመላው የኤጀንሲው ሰራተኞች ጋር በጋራ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ አድማሱ ማሞ የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኤጀንሲውን የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን፣ የ2010 በጀት ዓመት በኤጀንሲው የታቀዱ የግቦች አፈጻጸም፣የቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም፣የዓበይት ተግባራት አፈጻጸም፣በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተሰጡ ግብረ-መልሶች፣ሀገራዊ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት በማድረግ የታቀደው የኤጄንሲው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ፣ በኤጀንሲው የተደረጉ የስጋት ዳሰሳ ጥናት ሠነድ የኤጄንሲው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ለ2011 የኤጀንሲው ዕቅድ መነሻ ተደርጎ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ዳይሬክተሩ በ2011 በጀት ዓመት የታቀዱ ግቦችና ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ የተገልጋዮችና ባለድርሻዎችን ዕርካታ ለማሳደግ፣ ለውስጥና የውጭ ተገልጋዩች በዜጎች ቻርተር በተቀመጠ የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድ መሰረት አገልግሎት መስጠት፣ የሀብት አጠቃቀምና ውጤታማነት በማጎልበት ለኤጄንሲው የተመደበውን በጀት በፕሮግራም በጀት መርህ መሰረት ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀምና ስትራቴጂያዊ ግቦችን ማሳካት፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሪፎርም ሥራዎችን ማጠናከር፣ የመንግስት ግዥ አስተዳደር አፈፃፀምን ማሻሻል፣ የመንግስት ንብረት አስተዳደር አፈፃፀምን ማሻሻል፣የመንግስት ግዥ እና ንብረት አሰተዳደርና ኦዲትና ቁጥጥር ማጠናከር፣ የግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አወጋገድ አቤቱታዎች እና የጥፋተኝነት ሪፖርቶች ውሳኔ አሰጣጥ ማሻሻል፣ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን በማካተት ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ የሰው ሀብት አቅምን ማሳደግ፣ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የስራ አካባቢ ምቹነትን ማሳደግ መሆኑን በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዉ በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ማርታ እና የኤጀንሲው ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ የማጠቃለያ ንግግር አድርገው የጋራ ግንዛቤ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው የዉይይት መድረክ ላይ 110 የሚሆኑ የኤጀንሲዉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት