The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በህይወት እና በተግባቦት ክህሎት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በህይወት እና በተግባቦት ክህሎት ዙሪያ ለኤጀንሲው ባለሙያዎች በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ፡፡ ወ/ሮ ፍሬወይኒ ገ/እግዚአብሄር ከትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከል የሥርዓተ-ጾታ ባለሙያ የግንዛቤ ማስጨበጫ  ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ የሥልጠናውም ዓላማ ሰለህይወት እና ተግባቦት ክህሎት ምንነት፣ እነዚህን ክህሎቶች እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል እና ውጤቱም ጥሩ የሥራ ከባቢ አየር መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሰልጣኟ በስነ-ልቦናዊ ክህሎት ውስጥ ራስን ማወቅና ማክበር፣ በራስ መተማመን፣ ልበ-ሙሉነት እና ስለግብ የማስቀመጥ ክህሎት ያስረዱ ሲሆን፣ ራስን ማወቅ ለምን አስፈለገ? ራስን ማወቅ ማለት እንድ ሰው ስለራሱ ያለውን አእምሯዊ፣ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬና ድክመት አጠቃላይ ሁኔታ ማወቅ ማለት እንደሆነ፣ ራስን  የማወቅ  አቅም እንዴት  ማሳደግ እንደሚቻል፣ በራስ መተማመን ማለት ምን ማለት ነው? በራስ መተማመንን ለማሳደግ ቁልፍ ነጥቦች፣ ስለ ልበ-ሙሉነትና መገለጫዎቹ፣ እንዴት ማዳበር እንደሚቻልና ስለጥቅሞቹ፣ ግብ ማለት ምን ማት ነው? የግብ አይነቶች እና ስኬታማ ግብ ለመጣል የሚያግዙ ቅድመ ሁኔታዎች ምንድናቸው? የሚለውን በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡
በመቀጠልም ተግባቦት ምንድነው? ውጤታማ ተግባቦት እንዴት ማዳበር ይቻላል? ስለሂደቱ፣ ውጤታማ ተግባቦት ለመፍጠር ሰለሚያግዙ ክህሎቶች እና ጥቅሞች፣ሰለመመካከርና መደጋገፍ፣ ግብና ጠቀሜታ፣ ሰለውሳኔ አሰጣጥ ክህሎት ውጤታማነት፣ውሳኔ ለመወሰን ሰለሚያግዙ ሂደቶች እና ስልቶች ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡በተሰጠው ሥልጠናው ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች የተነሱና አስተያየቶችም የተሰጡ ሲሆን ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው ሥልጠና ላይ የኤጀንሲው ባለሙያዎች በንቃት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት