The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግንቦት 20 27ኛውን ዓመት በዓል በድምቀት አከበረ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግሥት ግዥና የንብረት ማስወገድ አግልግሎት ጋር በመተባበር 27ኛውን የግንቦት 20 በዓል ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አግልግሎት አዳራሽ በድምቀት አከበረ፡፡ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ግንቦት 20 ላለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ብዙ የድል ፍሬዎች ያገኘንባቸውን በማስታወስ በየዓመቱ የምናከብረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርዋና ዳይሬክተሯ በመቀጠልም በሁሉም ሴክተሮች አገራችን የለውጥ ጎዳና ላይ ያለች መሆኗንና እነዚህን መነሻ አድርገን  እንዴት እናጠናክራቸው በሚል ዝርዝር ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን ሁላችንም ኢትዮጵያ የሚለውን ይዘን የተቋምና የአገር ተልዕኳ ችንን መወጣት እንዳለብን አሳስበዋል፡፡አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አግልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ የግንቦት 20 ድል የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነትን ያከበረ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ መሠረት መጣሉን፣ ግንቦት 20 በፈጠረው አዲስ ምእራፍ ከአገሪቱ እድገት ጋር በተያያዘ የህዝቡ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን፣በዚህም ምክንያት የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በስፋት እየቀረቡ መገኘታቸውንና መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየተረባረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Participants of Ginbot 20 Meeting

በመቀጠልም ም/ዋና ዳይሬክተሩ ህዝቦች ማንነታቸው ተከብሮ በጋራ የሚኖሩበትን ስርዓት በመፍጠር በህዝቦች ሙሉ ፈቃድ ህገ መንግስታችንን በማጽደቅ አዲሲቷን ኢትዮጵያ መመስረቷን፣ህገ መንግስቱ ህዝቦች ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን የገለፁበት፣ በአዲስ መንፈስ የጋራ ግንባር ፈጥረው፣ ተከባብረውና ተጋግዘው አብረው ለመኖር፤ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር ቃል የገቡበት ሰነድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡በመጨረሻም የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤቶችና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍታት፣የአገራችንን ሠላምን በዘላቂነት አስጠብቆ የማስቀጠል አስፈላጊነትን አስረድተው የግንቦት 20 27ኛው ዓመት መሪ ቃል የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት፤ ለላቀ አገራዊ ስኬት መሆኑን በመጥቀስ አጠናቅቀዋል፡፡ከበዓሉ ታዳሚዎች የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ለተጠየቁ ጥያቄዎቸም መልስ በአግባቡ ተሰጥቷል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው  የግንቦት 20 27ኛው ዓመት በዓልን የሁለቱም መ/ቤት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በድምቀት አክብረው የዕለቱ ስብሰባ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ተጠናቋል፡፡


የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት