The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሮኒክ ግዥን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስትን ግዥ በኤሌክትሮኒክ (Electnonic Government Procurement) ስርዓት ሊጀምር መሆኑን የኤጀንሲው የግዥ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነብዩ ኮከብ አስታወቁ፡፡
ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንግስትን ግዥን በኤሌክትሮኒክ (Electnonic Government Procurement) ስርዓት ለማከናወን ፕሮጀክት ያቋቋመ ሲሆን የፕሮጄክቱ ማናጀር በቅርቡ ቅጥሩ የተፈጸመ እና የኮሚዩኒኬሽን አማካሪም በጨረታ አሸናፊው ተለይቶ ውል የመፈጸም ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የዚህን ፕሮጄክት አፈጻጸም ለመከታተል እና ለማቀናጀት 9 አባላት ያሉት ከሰባት የፌዴራል ተቋማት የተውጣጣ አስተባበሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን መ/ቤቶቹም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ይህ በኤሌክትሮኒክ የታገዘ የመንግስት ግዥ በዋናነት በሀገር ደረጃ ከሚመደበዉ በጀት ዉስጥ ከፍተኛዉን ድርሻ በቀጥታም ይሁን በተዘዋወሪ ለግዥ ስራ የሚዉል በመሆኑና የግዥ ሂደቱም ከሰው ንክኪ ውጭ በማድረግ ለሙስና እና ለኪራይ ሰብሰቢነት ተጋላጭነትን በእጅጉ እንደሚቀርፍ ይታመናል፡፡
ኤጀንሲው በቀጣይ የፕሮጄክቱን ጽ/ቤት ለማቋቋም፣ ተጨማሪ ባለሙያዎችን የመቅጠር፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ—ግብሮችን ለማዘጋጀትና ሙሉ በሙሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለዉ ገልጸዋል፡፡

በመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት