The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፎረም አደረጃጀትን በተመለከተ ሥልጠና ተሰጠ አዋጅ ቁጥር 1064/2010 የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ  ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመተባበር በሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፎረም አደረጃጀትን በተመለከተ ታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
አቶ ብርሃኑ ታደለ በፐብሊክ ሰርቪስ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ስለሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ሊሻሻል ሰለተፈለገበት ምክንያቶች በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚካሄደውን የምልመላና መረጣ ሥርዓትን በመሰረታዊነት በመለወጥና በአገር አቀፍ ደረጃ የሙያና የሥራ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት በመዘርጋት፣ እንዲሁም የመንግስት ሠራተኛው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ብዝሀነትን ያረጋገጠና ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለችውን እድገት ለማስቀጠል የሚያስችል ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባትና የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም በሰው ሃብት ሥራ አመራር ረገድ ያመጣቸውን ውጤቶች ለማጎልበትና ለማስቀጠል የሚያስችል ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም አሰልጣኙ አዋጁ 12 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በክፍል ሶስት አንቀጽ 19፣ በክፍል አራት ንኡስ ክፍል ሁለት አንቀጽ 42 እና በክፍል አምስት አንቀጽ 48 ላይ ለሴት ሠራተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ድንጋጌዎች መካተታቸውን፣ አንቀጽ 19/5 በሙከራ ላይ ያለ የመንግሥት ሠራተኛ በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ወይም በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ምክንያት ከሥራ የቀረ እንደሆነ ያልጨረሰውን የሙከራ ጊዜ ከሕመሙ ወይም ከጉዳቱ ከዳነበት ጊዜ አንስቶ እንዲጨርስ እንደሚደረግ፣ አንቀጽ 19/7 የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) ድንጋጌ ቢኖርም በወሊድ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ በሥራዋ ላይ ያልተገኘች የሙከራ ሠራተኛ የወሊድ ፈቃዷ እንደተጠናቀቀ የሙከራ ጊዜ እንድትጨርስ እንደሚደረግ፤ ሆኖም በሙከራ ሥራዋ ላይ ያልተገኘችበት ጊዜ ከአንድ ወር በታች ከሆነ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቷ በሥራ ላይ በቆየችበት ጊዜ ታስቦ እንደሚሞላላት፣ የወሊድ ፈቃድንም በሚመለከት ነፍሰጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት፣ በአጠቃላይ 120 ተከታታይ ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ ፈቃድ እንደሚሰጣት፣  ሴቶች በቅጥር፣ በደረጃ እድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡ወ/ሮ ሊዲያ ንጋቱ በፐብሊክ ሰርቪስ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት የስርዓተ ፆታ ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት የፎረም አደረጃጀትን በተመለከተ ፎረም ማለት ምን ማለት ነው? ለሴቶች በመ/ቤት /ፎረም መመስረት/ የሚኖረው ፋይዳ፣ በፌዴራል ተቋማት የሴቶች ሠራተኞች ፎረም ለማቋቋም ዝርዝር ዓላማ፣ በፌዴራል መንግስት ተቋማት የፎረም አስፈላጊነት፣ የፌዴራል መንግስት ተቋማት ፎረም አመሠራረት፣ የሴት ሠራተኞች ፎረም መተዳደሪያ ደንቡ ሲዘጋጅ በውስጡ የሚኖረው ይዘት የሚለውን በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለግማሽ ቀን የቆየው በሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፎረም አደረጃጀት በተመለከተ ሥልጠና ላይ የሁለቱም መ/ቤት ሃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡


የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት