The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ለኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ፡፡ ወ/ሮ መሠረት ማሞ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ በሥልጠናውም ከሰብዓዊ መብቶች መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ተነስተው ስለመብቶቹ ትርጉም፡- እነዚህ መብቶች መሰረታቸው የሰው ልጅ ክብርና ዋጋ ነው ለማለት የሚቻል ሲሆን የእነዚህ መብቶች ምንጭ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መሆኑንና ሰብዓዊ መብቶች በተፈጥሮ ያገኘናቸው መብቶችና ነጻነቶች ናቸው ቢባሉም ሕግ በበኩሉ እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ፣ እንዲተገበሩ እውቅ እና ጥበቃ እንዲያገኙ ለማስቻል ከፍተኛ ሚና እንዳለው አሰረድተዋል፡፡

በመቀጠልም አሰልጣኟ የሰብዓዊ መብቶች ታሪካዊ አመጣጥ፣ የሰብዓዊ መብቶች ባህሪያትና አመዳደብ፣ የሰብዓዊ መብቶች ገደቦች እና እገዳዎች፣ ሰብዓዊ መብቶችና የመንግስት ግዴታዎች፣የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ማስፈፀሚያና መከታተያ ሥርዓትና ሕጎች፣ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ይዘት የሰብዓዊ መብት እና የመልካም አሰተዳደር ትስስር/ቁርኝትን በሚመለከት ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡አቶ ታደሰ ተሰማ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ግንዛቤ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ሰለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ አሰራር ለልማት ማለት በየትኛውም የልማት ስራ ሂደት ውስጥ የአለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ማስከበር እና ማክበር በሚያስችል መንገድ አጣምሮ ማስኬድንየሚያረጋግጥ የአሰራር ስርአት መሆኑን፣ ስለድህነት ትርጉም፣ድህነት ከሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ ጋር ቁርኝት እንዳለው፣(ማህበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ መብቶች ጋር)፣ የሰብአዊ  መብቶች፤ ልማት እና ድህነት ቅነሳ ስላላቸው ግንኙነት በሰፊው ገልጸዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የዕለቱ ሥልጠና ተጠናቋል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት