የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ ከመላው የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር ህዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ማሰወገድ አገልገሎት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ–ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የስብሰባው ዓላማ በዚህ በ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ምን አቅደን? ምንስ ፈጸምን? የሚለውን ለመወያየትና በቀጣይ መሰረት ለማስቀመጥ መሆኑን ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ በዋናነት እንደሚታወቀው እቅድ ሶስት ሂደቶች (የዝግጅት፣ የትግበራና የማጠቃለያ ምዕራፎች) እንዳሉት እና ከነዚህም በመጀመሪያው የዝግጅት ምዕራፍ ብዙ ስራዎች እንደተሰሩና ማኔጅመንቱም ሰፊ ጊዜ ወስዶ ያለፈውን ገምግሞ ዝግጅቱን ወደ ሰራተኛው ማውረዱን፣ ከዕቅድ ዝግጅት ባለፈ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝቶ ሥልጠና መሰጠቱን መመሪያዎችንና የሥጋት ተጋላጮች ምንድናቸው? የሚሉት ታይተው መገምገማቸውንና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ወ/ሮ አበባ ዓለማየሁ የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኤጀንሲውን የ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ አመት የዕቅድ አፈፃፀምን በሚመለከት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ኤጀንሲው የ5 አመት ስትራቴጂያዊ እቅድ (ከ2008-2012) አዘጋጅቶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገብር ቆይቶ በ2011 በጀትዓመት ዕቅዱን እንደገና በመፈተሽ አሠራሩን ዘመናዊና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ የትኩረት መስኮችና ግቦችን በማሻሻል የግዥና የንብረት አስተዳደር ሥራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል የስራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን አሰረድተዋል፡፡