የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር የውይይት አካሄደ።

(ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመንግስት ግዥ ስርዓት ለአምራች ኢንዱስትሪው የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በሚመለከት ከአምራች ኢንዱስትሪ አመራር ጋር ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ የግዥ ስርዓቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው የፈጠረውን እድል በመጠቀም የሀገረ በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ማጎልብትና የገብያ ትሥስር መፍጠርን ያለመ ነው።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪን ማብረታታትና አቅም ማጎልበት እንዲሁም ገቢ ምርትን እንዲይተኩ ማስቻል መሆኑን ሲሆን ለዚህም ለሀገር በቀል ኢንዱስትሪው የሚያበረታታ የግዥ ስርዓት ተፈጥሯል ብለዋል። ክቡር አቶ መላኩ አያይዘውም የተፈጠረውን የግዥ እድል በአግባቡ ለመጠቀም አደረጃጀትን ማጠናከር፣ ባለሙያዎችን በእውቀትና በክሎት ማላቅ እንዲሁም በጥራትና በብዛት ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል የውይይቱን መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ሲሆኑ የሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች እንደተዘጋጁና የሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ የመንግስትን ግዥ መደገፍ መሆኑን አመላክተዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት በተለይም በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ 1333/2016 እና እሱን ለማስፈጸም በወጡ የህግ ማዕቀፎች ሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪውን የሚያበረታቱ፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የሚያሳድጉ እና ውድድርን የሚጨምሩ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የገበያ ትሥስር በመፈጠርና ውጤታማ የአምራች -ተጠቃሚ ሰንሰለትን በማጠናከር በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ትልቅ ሚና እንዳለውና አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማምረት በተጨማሪም በአሉብት ሆነው በአራቢነት መስራት እንደሚችሉም ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው በተለይም እሴትን ጨምረው ለሚያመርቱ ሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎች በጨመሩት እሴት ልክ ልዩ አስተያየት የሚያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። እንደ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጻ በግዥ ስርዓት የልዩ አስተያየት ዋና ዋና አላማዎች መንግስት የጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕውን ለማድረግ፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህልን ለማጎልበት መሆኑ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በክቡር ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበልና በዋና ዳይሬክተሯ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ምላሽና ማብራሪያ መደረኩ ፍጻሜውን አግኝቷል።






0 Comments